ከአሶሳ መንዲ በተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ በመውደቁ በአሶሳና በዙሪያው በሚገኙ ወረዳዎች ኃይል መቋረጡን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ እስማኤል ሙዘይን እንደገለፁት የኃይል ተሸካሚ ምሰሶው የወደቀው በምዕራብ ወለጋ ዞን መነሲቡ ወረዳ ቤንጉዋ ቀበሌ ነው።
በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶው ላይ ስርቆት ባይፈፀምም በመፈታታቱ የተነሳ አገልግሎት መስጠት አቅቶት መውደቁን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በዚህ የተነሳ በአሶሳ ከተማና በዙሪያው ባሉ ወረዳዎችና የገጠር ቀበሌዎች ከሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ኃይል መቋረጡን ገልፀዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የወደቀውን የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ለመጠገን የቴክኒክ ቡድን በሥፍራው ቢደርስም ምሶሶውን በነበረበት ሁኔታ መልሶ ለማቆም ረዘም ያሉ ሳምንታት እንደሚወስድ ሪፓርት አቅርቧል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ለበርካታ ቀናት በጭለማ ውስጥ እንዳይቆይ የሚያደርግ ቴክኒካዊ አማራጭ መፍትሔ ቀርቦ ከሪጅኑ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የድጋፍ ጥያቄ መቅረቡን ጠቁመዋል።
በቀረበው ጊዜያዊ መፍትሔ ክልሉ በጥቂት ቀናት ውስጥ በተፋጠነ ሁኔታ ኤሌክትሪክ እንደሚያገኝ ዳይሬክተሩ እምነታቸውን ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ የደረሰው ጉዳት እስኪጠገን ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅ አቶ እስማኤል ጥሪ አቅርበዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”