የኤሌክትሪክ ግሪድ ዲጂታላይዜሽን ማለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ ማስተላለፍና ማከፋፈል ሥርዓትን ዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የበለጠ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ዘመናዊ ማድረግ ነው። ይህ ሂደት ተለምዷዊውን የኤሌክትሪክ ግሪድ ከኢንተርኔት፣ ሴንሰሮች፣ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ ዳታ ትንተናና ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማዋሃድ እንደ “ስማርት አውታር” (Smart Grid) እንዲኖር የማድረግ ሂደት ነው።
ይህ አሰራር የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና የተጠቃሚዎችን ቆጣሪዎች በአንድ ዲጂታል ኔትወርክ በማገናኘት አጠቃላይ ስርዓቱ እርስ በእርሱ እንዲናበብና በራስ-ሰር (Automatically) እንዲቆጣጠር ያስችለዋል። በሌላ አገላለጽ፣ ዲጂታላይዜሽን የኤሌክትሪክ ግሪዱን “ባለ አእምሮ” ሥርዓት ያደርገዋል — ሥርዓቱ በራሱ መረጃ መሰብሰብ፣ መተንተንና በመተንተን ላይ ተመስርቶ ውሳኔ መስጠት ይችላል።
የግሪድ ዲጂታላይዜሽን ዋና ዋና አካላት
ስማርት ሜትሮች (Smart Meters)፦ በተጠቃሚዎች ቤት ወይም መስሪያ ቦታ የሚገጠሙ ዘመናዊ ቆጣሪዎች ሲሆኑ፣ የኃይል አጠቃቀም መረጃን በቅጽበት (Real-time) ለኃይል አቅራቢው ተቋም ይልካሉ።
ዲጂታል ማከፋፈያ ጣቢያዎች (Digital Substations)፦ የቮልቴጅና ፍሪኩዌንሲ መዋዠቅን በሴንሰሮች አማካይነት በሰከንዶች እጅግ አነስተኛ መዋዠቅ እንዳይፈጠር የሚቆጣጠሩና የሚያስተካክሉ ናቸው።
ራስ-ሰር ወይም አውቶሜትድ የማስተላለፊያ መስመር ቁጥጥር (Advanced Transmission line Management Systems)፦ በከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ብልሽት ሲከሰት በራሱ ጊዜ ችግሩን ለይቶ ኃይል በሌላ አቅጣጫ እንዲያገኙ የሚያደርግ አሰራር ነው።
የመረጃ ትንተና እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፦ የወደፊት የኃይል ፍላጎትን እና የአየር ጠባይ ለውጥን አስቀድሞ በመተንበይ ስርዓቱ ዝግጁ እንዲሆን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።
የግሪድ ዲጂታላይዜሽን ጥቅሞች
ብልሽቶችን በቅጽበት መለየትና በፍጥነት መጠገን፦ ቀደም ሲል የኤሌክትሪክ መስመር ሲቋረጥ ቴክኒሻኖች በአካል ተሰማርተው ቦታውን መፈለግ ነበረባቸው። በዲጂታላይዜሽን ስርዓት ግን ሲስተሙ ብልሽቱ የተከሰተበትን ትክክለኛ ቦታ እና ርቀቱን ወዲያውኑ ስለሚያሳይ የጥገና ጊዜን ያጥራል።
የኃይል ብክነትን መቀነስ (Loss Reduction)፦ በቴክኒክ ምክንያት በሙቀት መልክ የሚባክነውን ኤሌክትሪክ እንዲሁም ያለአግባብ የሚደረግ የኃይል ስርቆትን (Non-technical losses) በዲጂታል ቁጥጥር መግታት ያስችላል።
ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ማቀናጀት፦ የፀሐይና የንፋስ ኃይል እንደ አየር ጠባዩ ሁኔታ የሚዋዥቁ በመሆናቸው፣ ዲጂታል ግሪድ እነዚህን ተዋዥቅ የኃይል ምንጮች ከውሃ ኃይል ጋር ሳይረበሽ አቀናጅቶ ለመምራት ወሳኝ ነው።
የደንበኞችን እርካታ ማሳደግ፦ ደንበኞች የኃይል አጠቃቀማቸውንና እንዲከታተሉ ያስችላቸዋል።
የኃይል መረብ ዲጂታላይዜሽን የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ከተለመደው “ኃይል ማቅረብ” ሂደት ወደ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን የሚቋቋም (Resilient) የዲጂታል አገልግሎት የመቀየር ሂደት ነው። ይህ አሰራር ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ለኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት እና ለዜጎች እንግልት መቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው የኃይል ዘርፍ የወደፊት አቅጣጫ ተደርጎ እየተሰራበት ነው።