የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰጠውን አገልግሎት በጥናት ላይ ተመስርቶ ለማዘመንና የተጣለበት ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ በተቋሙ የኢትዮ ፓወር አካዳሚ የምርምርና ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢትወደድ ገብረአሊፍ ገለጹ፡፡
በደንበኞች እርካታ፣ በድርጅታዊ ባህል፣ በሠራተኞች የሥራ እርካታ እና ተሳትፎ ዙሪያ በኢትዮ ፓወር አካዳሚ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምርምርና የልማት ቡድን በጋራ የተከናወኑ ጥናቶች ለተቋሙ አመራሮች ቀርቧል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የጥናቶቹ ዓላማ፣ ስልትና ሞዴል፣ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎች፣ የናሙና አወሳሰድ፣ ንጽጽር፣ ግኝትና ምክረ ሀሳቦች በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ቀርበዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥንና አሰራርን ከማዘመን፣ የደንበኞችን እርካታ በየጊዜው ከመለካት፣ ከእውቀት አስተዳደር፣ ከሠራተኞች አቅም ግንባታ፣ ከኮንትራት አስተዳደር፣ የሚሰሩ ሥራዎችን ለባለድርሻ አካላት ከማሳወቅ፣ ወጥ ተቋማዊ ባህል ከመገንባት እንዲሁም ከቅንጅታዊ አሰራር አኳያ ክፍተቶች መኖራቸው ተነስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የጥናቱ ተሳታፊ ዶ/ር ጋዲሳ ለቺሳ እና አቶ ኤፍሬም አንዳርጌ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም ወደ ሀብት ለመቀየር የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ በጥናትና ምርምር መታገዝ አለበት፡፡

ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣትና በኃይል ዘርፍ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት በሚያደርገው ጥረት የሚታዩ ችግሮችን በጥናት አስደግፎ ለሥራ አመራሩ በማቅረብ ግብዓት ለመስጠት ጥናቶቹ መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለአመራሮች የቀረቡ ጥናቶች ተቋሙ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በመረጃና በሣይንሳዊ ጥናት ላይ ተመስርቶ እንዲፈታ በማገዝ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ ድርጅታዊ ባህልን ለማጠናከር እንዲሁም ብቁና ቁርጠኝ አመራርና ሠራተኛ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው አንስተዋል፡፡
ከሀገሪቱ እድገት ጋር ተያይዞ እየጨመረ ያለውን የኃይል ፍላጎት በአስተማማኝነት ለማረጋገጥ በጥናቱ ግኝት የተመላከቱ ጠንካራ ጎኖችን ለማጎልበት እንዲሁም የታዩ ክፍተቶችን ለማረም አመራሩ ኃላፊነቱን ወስዶ በቅንነት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
መሰል የዩኒቨርስቲዎችና ተቋማት ግንኙነት መሬት ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን ለማወቅ እንዲሁም ተቋማት በጥናትና ምርምር አካባቢ ያሉ ለውጦችንና እድገቶችን ተገንዝበው ውጤታማ ሥራ እንዲሰሩ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተነሱና ሊካተቱ የሚገቡ ግብዓቶችን በማካተት ተቋሙ በጥናቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግና እንደሚሰራ መምህራኑ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ ፓወር አካዳሚ የምርምርና ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢትወደድ ገብረአሊፍ በበኩላቸው ተቋሙ በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ ክፍተቶቹን ለማረም፣ አሰራሮችን በማዘመን ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ አሁን ያለበትን ቁመና በውል ተገንዝቦና ክፍተቶቹን ለይቶ በማረም ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ለማስመዝገብ ጥናቱ እንደመነሻ የሚያገለግል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ መረጃንና ማስረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔ አሰጣጥ አሰራርን ለመከተል እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ቢትወደድ በውይይቱ የተነሱ ግብዓቶች ተካተውባቸው ጥናቶቹ በቀጣይ ለተቋሙ ከፍተኛ አመራር እንደሚቀርቡም አብራርተዋል፡፡
ከአሁን ቀደም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተመለከተ እንዲሁም ሌሎች ጥናቶች ተጠናቀው ለሚመለከታቸው አካላት የቀረቡ ጥናቶች በአሁኑ ወቅትም በሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence – AI) ጨምሮ በሌሎች ስድስት አዳዲስ የምርምር ፕሮጀክቶች በተለያዩ ደረጃዎች ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
የተቋሙን አሰራር ማዘመን ደንበኛን በጥራት ማገልገል፣ የድርጅቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ፣ አሰራርን ማቀላጠፍ እና የሠራተኛን እንዲሁም የደንበኞችን እርካታ ማሳደግ በመሆኑ በጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል፡፡




