የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽነት (accessibility) እና አስተማማኝነት (dependability) የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ሞተሮች እና የዘመናዊ እድገት መለኪያ ጠቋሚዎች ናቸው። ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እና ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሠረቶች ናቸው።
በልማት ኤኮኖሚክስ እና በኃይል ፖሊሲ ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አስተማማኝ እና ፍትሐዊ የኃይል አቅርቦት የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የሰው ኃይል አቅምን ለማጎልበት እና የተቀናጀ ሀገራዊ ዘላቂ የልማት ለማሳካት አስፈላጊ ግብዓት ነው።
1. የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት (Accessibility)
የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ማለት አገልግሎቱን በከተማም ሆነ በገጠር ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በፍትሐዊነት፣ በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ማድረስን የሚያመለክት የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ ጽንሰ ሀሳብ ነው።
የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ወደ ገጠር እና አዳዲስ ከተሞች መስፋፋት የጤና ተቋማት መድኃኒቶችንና ክትባቶችን በማቀዝቀዣ እንዲጠብቁ፣ ትምህርት ቤቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲደገፉ እና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በአስተማማኝንት እንዲሠሩ በማድረግ ማህበራዊ አገልግሎቶች እስዲስፋፉ ያደርጋል።
ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ እና ለገጠር አነስተኛ ንግዶች መፋጠንም በር ይከፍታል።
2. የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስተማማኝነት (Dependability)
የኃይል ተደራሽነት ሀገራዊ ፋይዳ የሚኖረው የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ጥራቱን የጠበቀ፣ በቮልቴጅ መዋዠቅ ምክንያት መሣሪያዎችን የማይጎዳ እና ያለበቂ ምክንያት በተደጋጋሚ የማይቋረጥ ሲሆን ነው።
የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት ፋብሪካዎች፣ የማምረቻ ተቋማት እና የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በበቂ ምክንያት ካልሆነ በቀር የኃይል መቋረጥ ሳይገጥማቸው በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱና የምርት ብክነትን እንዲቀንሱ ያስችላቸዋል።
ሆስፒታሎች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባልተቋረጠ የኃይል አቅርቦት ሥራቸውን ለማከናወን ያስችላቸዋል፡፡
ስለሆነም የኃይል አቅርቦት ተደራሽነት እና አስተማማኝነት ለማህበረ – ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መሳለጥ የማይለያዩ የኃይል ዘርፍ ምሰሶዎች መሆናቸውን እንረዳለን። የኃይል ተደራሽነትን ማስፋፋት የዜጎችን ማህበራዊ ፍላጎት ሲመልስ የአገልግሎቱን አስተማማኝነት ማረጋገጥ ደግሞ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት ያጎለብታል።
ዘመናዊ የኃይል ማስተላለፊያ እና ማሰራጫ መሠረተ ልማቶችን መገንባት፣ ስማርት ግሪድ (Smart Grid) ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን (የውሃ፣ ነፋስ፣ ፀሐይ እና ጂኦተርማል) በስፋት ማቀናጀት የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግም ሆነ አስተማማኝነቱን ለማረጋገጥ ቁልፍ መፍትሔዎች ናቸው።