በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት በየዓመቱ ከሚደርስባቸው የጎርፍ አደጋ እና መፈናቀል እየጠበቃቸው መሆኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሃይድሮሎጂ እና ውኃ ሀብት ተባባሪ ፕሮፌሰር ደመላሽ ወንድምአገኘሁ (ዶ/ር) ገለፁ።
ደመላሽ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት ለረጅም ጊዜ የታችኞቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት በተለይም የሱዳን እና የግብፅ ሕዝቦች በክረምት ወቅት ለጎርፍ አደጋ፣ ለንብረት ውድመት እና መፈናቀል ይዳረጉ ነበር።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት አፈር በከፍተኛ ጎርፍ ተጠርጎ እንዳይወስድ በማድረግ የታችኞቹ ሀገራት ውሃውን እና አፈሩን በተሻለ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙበት እያገዛቸው መሆኑን አብራርተዋል።
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም የግብፅ ምሁራን የውኃ መጠን ማነስንና የጎርፍ አደጋን አስመልክቶ የሚያሰራጩት የተቀራረኑ መረጃዎች ዋነኛ ምክንያት ኢትዮጵያ እንዳታድግ እንዲሁም ከዚህ በኋላ በወንዙ ላይ ተጨማሪ ግድብ እንዳትገነባ ከመፈለግ የመነጨ እንጂ ግድቡ ከጎርፍ አደጋ እየታደጋቸው መሆኑን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አለመኖሩን በተለያዩ ጊዜያት በግድቡ ላይ በተደረጉ ጥናቶች መረጋገጡን የጠቆሙት ደመላሽ (ዶ/ር) የግድቡ መገንባት ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር የማድረግ ጥቅም እንዳለውም አብራርተዋል።
የታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት በግድቡ ላይ ከእውነታ የራቁ አሉታዊና አፍራሽ ቅስቀሳቸውን ወደ ጎን ትተው ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተባብረው ቢሰሩ የተሻለ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል፡፡