የተቋሙን የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ተጠቃሚ የሚያደርግ የብድር አቅርቦት ስምምነት ተፈረመ

የተቋሙን የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ተጠቃሚ የሚያደርግ የብድር አቅርቦት ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሥራ መሪዎቹና ሠራተኞቹ የረጅም ጊዜ የብድር አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ከኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ጋር ተፈራርሟል፡፡

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደርቤ አስፋው ተፈራርመዋል፡፡

የተቋሙ የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ ስለስምምነቱ እንደተናገሩት ተቋሙ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የሚፈጥረው አጋርነት የሠራተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከመፍታት ባሻገር ለወደፊት የፕሮጀክት ሥራዎች ማስፈፀሚያ የሚሆን የፋይናንስ ምንጭ ለማመቻቸት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

ስምምነቱ ለረጅም ጊዜ በቤት እጥረት እና በገበያ ላይ ባለው የዋጋ ንረት ምክንያት የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ለነበሩ ሠራተኞች ትልቅ እፎይታን የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ሥምምነቱ የሠራተኞችን የመበደር እና የመክፈል አቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ በቀጣይ የአፈፃፀም መመሪያ ተዘጋጅቶለት ወደ ሙሉ ትግበራ ሲሸጋገር ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከተለያዩ ባንኮች ጋር የሚደረጉ የትብብር ሥራዎች ተቋሙ ለሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች አጋዥ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ደመረ ወደፊትም የፋይናንስ አቅሙን ለማጎልበት የሚያስችሉ መሰል ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ የተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባንኪንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ እንደገለፁት የመግባቢያ ሥምምነቱ የሁለቱን ተቋማት ሠራተኞች የሚያገናኝና የረጅም ጊዜ አጋርነትን የሚፈጥር ነው።

ስምምነቱ የተቋሙ ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ለቤት፣ ለተሽከርካሪ እንዲሁም ለተለያዩ የግል አስቸኳይ ፍላጎቶቻቸው የሚሆን የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ በማመቻቸት ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ለማስቻል ያለመ ነው።

ባንኩ እስካሁን ድረስ ያለ ምንም መያዣ እስከ 63 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ብድር ለተለያዩ የተቋማት ሠራተኞችና የህብረተሰብ ክፍሎች ማቅረቡንም ጠቁመዋል።

የሥምምነት ማዕቀፉ በሁለቱም ወገኖች በተዋቀሩ የቴክኒክ ቡድኖች አማካኝነት ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚሸጋገርና ሠራተኞችም በአነስተኛ የወለድ መጠን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

Scroll to Top