“ተቋሙ የሚያካሂዳቸው ግዥዎች ከህግ ጥሰትና ከሙስና የጸዱ መሆን አለባቸው” ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

“ተቋሙ የሚያካሂዳቸው ግዥዎች ከህግ ጥሰትና ከሙስና የጸዱ መሆን አለባቸው” ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግዥ ሂደቶች ከሕግ ጥሰትና ከሙስና የጸዱ፣ በረጅም ጊዜ ዕቅድ ላይ የተመሠረቱ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሊሆኑ እንደሚገባ  የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አሳሰቡ።

ለተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተቋሙ በሚያከናውናቸው የግዥ ሂደቶችና የአሠራር ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተካሂዷል።



የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ እንደገለጹት ሕግና መመሪያን የተከተለ የግዥ አሠራር ሂደት ለተቋማዊ ዕድገትና ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ ነው።

የግዥ ዘርፉ ከፍተኛ ሥጋት ያለበትና ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ስለ አሠራሩ የጋራ መረዳት ሊኖራቸው እንደሚገባ ሥራ አስፈጻሚው አስገንዝበዋል።

በተቋሙ ግልጽና ቀልጣፋ የግዥ ሥርዓትን በመዘርጋት ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ከዚህ ቀደም ሲተገበሩ የነበሩ አሠራሮችንና ሂደቶችን በጥልቀት ፈትሾ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ በጥድፊያ የሚፈጸሙ ያልታቀዱ ግዥዎችን ሙሉ በሙሉ በማስቀረት ሁሉም የግዥ ሂደቶች የረጅም ጊዜ ዕቅድን መሠረት አድርገው እንዲከናወኑ መሥራት ያስፈልጋል።

በግዥ ሂደት ላይ የሚፈጠሩ ጥቃቅን ድክመቶች በሜጋ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ጫና በማሳደር ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት በመሆን ተቋማዊ ግቦችን እንደሚያስተጓጉሉም ነው ያስረዱት፡፡

በሌላ በኩል ከተቋሙ ሪፎርም ወዲህ የተጀመሩ በጎ ጅምሮች ቢኖሩም አሁንም ድረስ ያልተሻገርናቸው ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ኢንጂነር አሸብር  ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የግዥ ሥራውን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በግዥ ሂደት የሚታዩ መዘገየቶችንና የአሰራር ክፍተቶችን ለመፍታት እንዲሁም ዘመናዊ አሰራር ለመዘርጋት ተቋሙ የጀመረውን የዲጂታል ግዥ ሥርዓት  አጠናቆ ስራ ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የግዥ አሠራር ውጤታማነት የጥቂት የሥራ ክፍሎች የቤት ሥራ ሳይሆን የሁሉም አመራርና ሠራተኛ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስገንዝበዋል።

በመሆኑም የተቋሙን ግቦች ለማሳካት ሁሉም የሥራ ክፍሎች በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

Scroll to Top