የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጥራትን ማሻሻል

የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጥራትን ማሻሻል

በአንድ ሀገር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚጫወተው ሚና ወደር የለውም። የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢንዱስትሪዎች መንቀሳቀስ፣ ለንግድ ተቋማት መስፋፋት፣ ለጤና እና ትምህርት አገልግሎቶች መዘመን እንዲሁም ለዜጎች የዕለት ተዕለት ህይወት መሻሻል ዋነኛ መሰረት ነው።
ይሁንና ዘላቂና ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ማስፋፋት እና የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻል ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች ናቸው፡፡
 
የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ማለት አገልግሎቱ ያልደረሳቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም በገጠርና ከከተሞች ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ከዋናው ግሪድ የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ማለት ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ አገልግሎቱን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በፍትሐዊነት በማድረስ ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡
 
ተደራሽነትን ለማስፋት የሚሰሩት ሥራዎች ዋናውን ግሪድ ከመጠቀም በተጓዳኝ ከግሪዱ ጋር በቀላሉ ለመገናኘት የማይችሉ አካባቢዎችን አነስተኛ በሆኑ የፀሐይና የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች (Mini-Grids/Solar Home Systems) መጠቀምን ያካትታሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ቀድሞ ወዳንተዳረሰባቸው አዳዲስ የገጠር አካባቢዎች ሲደርስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲስፋፉ፣ የወጣቶች ስራ ዕድል እንዲፈጠር እና የግብርና ምርቶች እሴት እንዲጨመርባቸው በር ይከፍታል።
 
የኃይል አቅርቦት ጥራትና አስተማማኝነት መሻሻል
የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ተደራሽ ስለሆነ ብቻ የኃይል ዘርፉ ግብ ተሳካ ሊባል አይቻልም። ከዚህ ባልተናነሰ ለተጠቃሚዎች የሚቀርበው ኃይል ጥራቱን የጠበቀ እና አስተማማኝ ሊሆን ይገባል። በተደጋጋሚና ያለማሳሰቢያ የሚቋረጥ ኤሌክትሪክ ፋብሪካዎች በአግባቡ እንዳያመርቱ፣ ምርትን እንዲባክን፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎታቸው እንዲስተጓጎል፣ እንዲሁም የንግድ ተቋማትን እንዲከስሪ ሊያደገርግ ይችላል፡፡
 
የኃይል አቅርቦት ጥራትና አስተማማኝነት ሲጓደል የቮልቴጅ መዋዠቅ በቤቶችና በኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል፡፡ በመሆኑም የኃይል አቅርቦት መኖር ብቻ የጥራትና አስተማማኝነት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው የሆነው በእነዚህ ጉልህ ምክንያቶች ነው፡፡
 
ተደራሽነትን ለማስፋፋትና ጥራትን ለማሻሻል ምን ዓይነት ስልታዊ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው?
1.      ያረጁ የማስተላለፊያ መስመሮችንና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን (Substations) ማደስ እና አቅማቸውን ማሳደግ፤
 
2.    የራስ ሰር ወይምአውቶሜትድ ስርዓቶችን መዘርጋትና ስማርት ሜትሮችን በመትከል ብልሽቶችን በቅጽበት መለየትና የኃይል ብክነትን መቀነስ፤
 
3.    የታዳሽ ኃይል ምንጮች አሰባጥሮ በመጠቀምየኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝ ማድረግ፤
 
4.    ዘርፉን ለማሳደግ በመንግስት ላይ የሚኖረውን  የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ጫና ለመቀነስ የግል አልሚዎች በኃይል ማመንጨትና ማስተላለፍ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ማበረታታት፤
 
በአጠቃላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋት የዜጎችን መሰረታዊ የማህበራዊ ህይወት ፍላጎት የሚመልስ “የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ሽፋን” ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል የሀገርን የኢንዱስትሪና የንግድ ተወዳዳሪነት የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ይገባል።
 
ሁለቱንም ጎን ለጎን አቀናጅቶ መስራት ሀገራችን ለያዘችው የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እና ዘላቂ ልማት ትልቅ የብርሃንና የኃይል መንገድ ይሆናል።

Scroll to Top