የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

በአዲሱ በጀት ዓመት የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ምጣኔ ለማሳደግ በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንደሚደርጉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቁ፡፡

የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በህዝብ ውክልና ሥራ ለተሰበሰቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 15 የሚሆኑ አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያ እና ማስተላለፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይጀመራል፡፡

የሀገሪቱ የኃይል ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደ ህዳሴና ኮይሻ ያሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት፣ በአዳዲስ ፕሮጀክቶች ከወሰንና ካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ዝርፊያ የኃይል ተደራሽነትን ከመጉዳቱ በላይ ዘርፉን ወደ ኋላ እየጎተተ ይገኛል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መሠረት ልማቶችን በመጠበቅ የሀገርን ሀብት ከብክነት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ በበኩላቸው ተቋማቸው ከኃይል ፍላጎትና ጥራት እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

በበጀት ዓመቱ ከ 100 በላይ ከተሞችን የኃይል ተጠቃሚ የሚያደርጉና የኃይል መቆራረጥን የሚቀርፉ የማሻሻያ ፕሮጀክቶች ይተገበራሉ ብሏል።

በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 17 የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች በያዘነው በጀት ዓመት ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ ተመልክቷል።

ከክፍያ ጋር የተያያዙ እንግልቶችን ለማስቀረት የዲጂታል የክፍያ ዘዴ መመቻቸቱና ዲጂታል ቆጣሪዎችን በመጠቀም የቅድመ ክፍያ አገልግሎት በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ተቋሙ ገልጿል።

ከኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትና የኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ህብረሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰሩ ሁለቱ ተቋማት አረጋግጠዋል።

በቀጣይ ሶስት አመታት የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የአዳዲስ የኃይል ምንጮችና ማሰራጫዎች ግንባታ እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል።

የመረጃ ምንጫችን የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top