ማህበሩ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

ማህበሩ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአዳማ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የተጠናቀቀውን የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለጉባኤው ያቀረቡት የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ክፍሌ በበጀት ዓመቱ በጡረታ እና በሞት ለተለዩ የማህበሩ አባላት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈፀሙን ተናግረዋል።

ዲፕሎማ የትምህርት ዝግጅት ኖሯቸው ትምህርታቸውን ያሻሻሉ የተቋሙ ሠራተኞች የዲፕሎማ የስራ ልምዳቸውን ታሳቢ በማድረግ የዲግሪ ትምህርት ዝግጅት የሚጠይቁ የስራ መደቦች ላይ እንዲመደቡ መደረጉን ተናግረዋል።

የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማሳደግም በቅጥር ወቅት 30 በመቶ ዕድል ለሴቶች መሰጠቱን ገልፀዋል።

እንደ አቶ መኮንን ገለፃ በህብረት ስምምነቱ መሠረት በደረጃ ዕድገት እና በትምህርት ዕድል ሴቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

የማህበሩን የገቢ አቅም ከማሳደግ አንፃር የተለያዩ ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ በ2012 በጀት ዓመት አራት ሚሊዮን ብር የነበረውን የማህበሩ ሀብት በ2016 በጀት ዓመት መገባደጃ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ተችሏል።

የማህበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ኃይሉ ወልዴ በበኩላቸው በተለያዩ  ምክንያቶች በተጓደሉ የምክር ቤት አባላት የተተኩ  አዲስ አባላትን ለምክር ቤቱ ይፍ አድርገዋል።

ማህበሩ ዛሬ እና ነገ በሚያከናውነው መርሐ ግብር የ2016 በጀት ዓመት የፊስካል እና የበጀት አፈፃፀም እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ገምግሞ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top