የብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ፕሮጀክት ግንባታን በሚቀጥለው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ የዲጂታላይዜሽን እና አቅም ማሻሻል ፕሮጀክት አንድ ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ወ/ጊዮርጊስ እንደገለጹት
የመቆጣጠሪያ ማዕከሉ ህንጻ ግንባታ የስትራክቸር ስራ 98 በመቶ፣ የብሎኬት ሥራው 75 በመቶ እንዲሁም የልስን ስራው 47 በመቶ ደርሷል።
በማዕክሉ ውስጥ የሚተከሉት የግሪድ መቆጣጠሪያ ሲስተሞች ፍተሻ በኮንትራክተሩ ፋብሪካ ውስጥ መከናወን መጀመሩን አቶ በኃይሉ ተናግረዋል።
በማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚተከሉ የመረጃ ማሰባሰቢያ መሳሪያዎች፣ የኮሙዩኒኬሽን ዕቃዎቸ እንዲሁም ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሚያገለግሉ ፋየርዎሎች የፍብሪካ ፍተሻ መከናወኑንም ገልጸዋል፡፡
ቀይ ባህር ላይ ባጋጠመ የባህር ትራንስፖርት ስጋት ምክንያት የግንባታው አንዳንድ ሥራዎች የመዘግየት ችግር እንደገጠማቸው ኃላፊው ተናግረዋል።
እንደ አቶ በኃይሉ ገለጻ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ፕሮጀክቱን ግንባታ በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከኮንትራክተሩና አማካሪ መሀንዲሱ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
በዚህም አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም 62 በመቶ መድረሱንና አጠቃላይ የግንባታ ሥራውን እስከ ሐምሌ 2017 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አቶ በኃይሉ ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በዋነኛነት ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ የSCADA/EMS ሶፍትዌሮችን መጠቀም ከማከፋፈያ እና ከኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ጋር ወቅታዊ መረጃዎችን በማሰባሰብ የኦፕሬሽን ሥራዎችን አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማከናወን የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ ከሳይበር ጥቃት ሊከላከል የሚያስችል የሴኩሪቲ ሲስተም እንደሚኖረው የጠቆሙት ኃላፊው ለኦፕሬተሮች የሚሆን የመኖሪያ ቤት ግንባታም በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ፕሮጀክቱ በሥራ ላይ ካሉት የኃይል ማመንጫዎችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች በተጨማሪ ወደፊት የሚገነቡትን የኃይል መሰረተልማቶች ታሳቢ በማድረግ እየተገነባ ይገኛል።
የማዕከሉ መገንባት የሲስተም መዋዠቅን በመቀነስ የኃይል አቅርቦት ጥራትን ለማሻሻል ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ፕሮጀክት ከፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ (AFD) በተገኘ ብድር እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተመደበ 197 ሚሊየን ብር እና 62 ነጥብ 6 ሚሊየን ዩሮ በጀት በመገንባት ላይ ይገኛል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”