በዓለም ባንክ ብድር የሚተገበረው የኃይል ዘርፍ ሪፎርም፣ ኢንቨንስትመንት እና ሞደርናይዜሽን ፕሮግራም በእንግሊዝኛ ምዕፃሩ (PRIME ) የተሰኘው ፕሮግራም ይፋ ተደረገ።
ፕረግራሙ ዘርፈ ብዙ የኢነርጂ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ያለመ ነው።
በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ ላይ የፋይናንስ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው እንደገለፁት ለኢነርጂ ዘርፍ የሪፎርም ትግበራ በዓለም ባንክ በኩል 1.5 ቢሊዮን ዶላር ተመድቧል።
የኢነርጂ ዘርፍ ልማት በመንግሥት ልዩ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ የተመደበውን መዋዕለ ንዋይ ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አበበ ዘሪሁን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ አበበ እንደገለፁት በባንኩ ብድር የሚተገበረው የኃይል ዘርፍ ሪፎርም፣ ኢንቨንስትመንት እና ሞደርናይዜሽን ፕሮግራም በእንግሊዝኛ ምዕፃሩ (PRIME )ዘርፈ ብዙ የኢነርጂ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ያለመ ነው።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ የኦፕሬሽን አቅምን እና የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግ ያግዛል።
የሀገሪቱ ግማሽ ያህል ዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደማያገኙ የገለፁት አቶ ጎሳዬ ፕሮጀክቱ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የኢነርጂ እና ነዳጅ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክትር ወ/ሮ ሰሃረላ አብዱላሂ በበኩላቸው እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ጥራት ያለው የኤሌክትሪክ አቅርቦት እውን ለማድረግ ይረዳል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተጀመረው የፕራይም (PRIME) ፕሮጀክት የኢነርጂ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያግዝ በመሆኑ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ሥራ በተቀናጀ መልኩ እንደሚመሩ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የኢነርጂ ስፔሻሊስት አቶ አብዱልሃኪም ሙሐመድ በበኩላቸው በዓለም ባንክ ፋይናንስ የሚደረገው የኢነርጂ ሪፎርም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ለማከናወን የታቀደ ነው።
በስካይ ላይት ሆቴል በተከናወነው የማስጀመሪያ መርሃግብር የፋይናንስ ሚኒስቴር፣የኢነርጂ እና ነዳጅ ባለስልጣን፣ የዓለም ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፋተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”










