የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትን ስርቆት ለመከላከል አስተዳደሩ እየሰራ ነው

የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትን ስርቆት ለመከላከል አስተዳደሩ እየሰራ ነው

የወራቤ ከተማ አስተዳደር በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ የሚፈጸምን ስርቆት ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

የከተማ አስተዳደሩ የፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አክመል ጀማል እንደገለጹት በኢነርጅ አዋጅ 810/2006 እና በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ደህንነት ለመጠበቅ በወጣው አዋጅ 464/97 መሠረት የከተማ አስተዳደሮች የመሰረተ ልማት ስርቆትን የመከላከል ኃላፊነት አለባቸው።

ይህን መሠረት በማድረግም በወራቤ ማከፋፈያ ጣቢያና በከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ታወሮች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶችን በመከላከል በኩል የጸጥታ አካላት በቅንጅት እየሰሩ ይገኛል ብለዋል።

የመሠረተ ልማት ስርቆቱን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ስርቆቱ ተፈጽሞ ሲገኝ በአዋጁ መሠረት በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በዚህም በልዩ ሁኔታ ከ15 ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ በመመስረት ለፍርድ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽ/ቤት የታክቲክ ምርመራ አስተባባሪ ረዳት ኢንስፔክተር ራህመቶ ሙስጠፋ በበኩላቸው የማከፋፈያ ጣቢያው ሲገነባም ሆነ ከተገነባ በኋላ ስርቆት እንዳይፈጸም ፓሊስ ከሕብረተሰቡ ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአካባቢው ማህበረሰብ የአውጫጭኝ ሥርዓት መሰረት ስርቆት ሲፈጸም አጥፊዎች ላይ ክትትል በማድረግ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀዋል፡፡

በዚህም የታወር ብረቶች ላይ ስርቆት የፈጸሙ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ከአምስት ዓመት እስከ ስድስት ዓመት በሚደርስ እስራት መቀጣታቸውንና የሰረቁትን ብረትም ለጣቢያው መመለሱን ተናግረዋል።

ረዳት ኢንስፔክተር ራህመቶ አክለውም በአሁኑ ወቅትም ከማከፋፊያ ጣቢያው ኬብል ገመድ የሰረቀ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በኮሚኒቲ ፖሊሲንግ አማካኝነት ሕብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ችግሩን በኃላፊነት እንዲከላከል እየሰራን ነው የሚሉት ረዳት ኢንስፔክተር ራህመቶ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸም ስርቆት በሕብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ከግምት በማስገባት ከሌሎች መዝገቦች ቅድሚያ በመስጠት አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

አስተዳደሩ በሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ አሁን ላይ ማህበረሰቡ ለኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ጥበቃ የሚሰጠው ትኩረት በማደጉ አሁን ላይ ችግሩ እየቀነሰ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top