ለፕሮጀክቶች አፈፃፀም ፈተና የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ለፕሮጀክቶች አፈፃፀም ፈተና የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በተያዘላቸው መርሀ ግብር መሰረት ለማከናወን የታወር አካላት ስርቆት፣ የወሰን ማስከበር እና የፀጥታ ችግሮች ፈተና እንደሆኑበት የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በዘርፉ የአፈፃፀም ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ታረቀኝ እንዳስታወቁት በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ታቅዶ ሁለቱን ብቻ ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ የቡታጅራ – ወራቤ፣ ባህርዳር – ወልዲያ፣ ደጀን – ደብረ ማርቆስ፣ አዘዞ – ጭልጋ፣ የአዋሽ – ወልዲያ የባቡር ኃይል አቅርቦት ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲሁም የኮተቤ ጊቢ የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ታቅዶ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከቡታጅራ- ወራቤ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲሁም ከኮተቤ ግቢ የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች ውጪ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ አቶ አክሊሉ አስታውቀዋል፡፡

በዕቅዳቸው መሰረት ያልተጠናቀቁ አራቱ ፕሮጀክቶች ከ80 ነጥብ 7 እስከ 96 ነጥብ 4 በመቶ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ መድረሳቸውንም አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ አክሊሉ ገለጻ የወሰን ማስከበር፣ የታወር አካላት ስርቆት እና የጸጥታ ችግሮች ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንዳይጠናቀቁ ምክንያት ሆነዋል፡፡

የወሰን ማስከበር ችግሮችና የታወር አካላት ስርቆት ባለፈው በጀት ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብለው ከነበሩ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በግንባታ ላይ በሚገኙ ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይም ይስተዋላል።

ለፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ፈተና የሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት በየደረጃው ከሚገኙ የመስተዳደር አካላት፣ የጸጥታ ኃይሎች እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ቢካሄዱም ባለድርሻ አካላታ መግባባት ላይ በተደረሰው መሰረት በቁርጠኝነት ወደ ተግባር ባለመግባታቸው ውጤት ሊመጣ አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የሥራ ተቋራጮች አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን፣ ከውጭ የሚገቡ የፕሮጀክት ዕቃዎች የባህር ላይ ጉዞ መዘግየት እና የግንባታ ግብዓቶች እጥረት ተቋሙ በዕቅድ የያዛቸውን ሥራዎች በአግባቡ እንዳያከናውን ተፅዕኖ እያሳደሩ ካሉ ተጨማሪ ችግሮች መካከል እንደሚጠቀሱም አቶ አክሊሉ አመልክተዋል፡፡

በፕሮጀክቶች የግንባታ ሥራ ላይ እያጋጠሙ ያሉ የተለያዩ ችግሮች ለፕሮጀክቶች አፈፃፀም ፈተና ከመሆናቸውም ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪዎች እየዳረጉት እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር የሚኖራቸውን ፋይዳ በመረዳት ለመሠረተ ልማቱ ጥበቃ ከማድረግ ጀምሮ ለአፈፃፀም ፈተና የሆኑ ችግሮች እንዲፈቱ ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top