የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለመጨመር የሚያስችል የብሬከር ቅያሪ ተከናውኗል

የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለመጨመር የሚያስችል የብሬከር ቅያሪ ተከናውኗል

በሆሳዕና ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያን የመቆጣጠሪያ ክፍል የአቅም ማሳደግና ማሻሻል ሥራ መከናወኑን የጣቢያው ኃላፊ ገለጹ።

ኃላፊዋ ወ/ሮ ማህደር ገብረ መስቀል እንደገለጹት በ1978 ዓ.ም የተገነባው የሆሳዕና ማከፋፍያ ጣቢያ በአንድ ትራንስፎርመር በ132 ኪሎ ቮልት አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በተደረገለት ማሻሻያ በሦስት ትራንስፎርመር ወደ 230 ኪሎ ቮልት አድጓል።

ሆኖም በብሬከሩ ምክንያት የሚያጋጥመውን የኃይል መቆራረጥን ለማስወገድና የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያስችል የብሬከር ቅየራ ሥራ ተከናውኗል።

ቀደም ሲል የነበረውን የ33 ኪሎ ቮልት መቆጣጠሪያ ብሬከር በጋዝ በሚሰራ ጂ.አይ.ኤስ (Gas Insulated System) መቆጣጠሪያ በመቀየሩ የጣቢያውን የቁጥጥር ሥራ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ለማከናወን ማስቻሉን ኃላፊዋ ተናግረዋል።

የጂ.አይ. ኤስ መቆጣጠሪያ ብሬከር ቅየራው በአንድ ላይ ይወጡ የነበሩ ሁለት ወጪ መስመሮች በተናጠል እንዲወጡ ከማድረጉም ባሻገር የ33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮችን ቁጥር ከአራት ወደ ስድስት ከፍ ማድረጉን አብራርተዋል።

ሁለቱ መስመሮች በአንድ ላይ ወጪ በሚሆኑበት ጊዜ ችግሮች ሲያጋጥሙ ጥገና ለማካሄድ የኃይል መቆራረጥን ያስከትል እንደነበረ አስታውሰዋል።

የተከናወነው የብሬከር ቅየራ የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለመጨመር የሚያግዝ በመሆኑ ተጨማሪ የኃይል ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን ወ/ሮ ማህደር ተናግረዋል።

በጣቢያው የኦፕሬሽን ቴክኒሽያን የሆኑት አቶ ብርሀኑ ፀጋዬ በበኩላቸው ቀደም ሲል የነበረው ብሬከር ችግሮች ሲያጋጥሙ የጥገና ሥራ ለማከናወን ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድ እንደነበር አስታውሰዋል።

የመቆጣጠሪያው መቀየር የኃይል መቆራረጥንና በጥገና ሥራዎች ላይ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን እንደሚረዳም ነው ባለሙያው የተናገሩት።

የሆሳዕና ማከፋፍያ ጣቢያው በሦሥት ትራንስፎርመሮች 175 ሜጋ ቮልት አምፒዬር የመጫን አቅም አለው።

ማከፋፍያ ጣቢያው 132 ኪሎ ቮልት ከጊቤ አንድ እንዲሁም ከወልቂጤ ማከፋፈያ ጣቢያ ደግሞ 230 ኪሎ ቮልት የሚቀበል ሲሆን ባለ 15 ኪሎ ቮልት 7 እና ባለ 33 ኪሎ ቮልት 3 ወጭ መስመሮች አሉት።

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top