ለዘመን መለወጫ በዓል የኃይል አቅርቦት ቅድመ ዝግጅት ተጀምሯል

ለዘመን መለወጫ በዓል የኃይል አቅርቦት ቅድመ ዝግጅት ተጀምሯል

በአዲስ አበባ ከተማ በበአል ወቅት በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ሊከሰት የሚችልን ከፍተኛ የኃይል ጭነት ለመቆጣጠር ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በዘርፉ የማዕከላዊ 3 ሪጅን እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የምዕራብ፣ ደቡብ እና ሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክቶች የጋራ ስብሰባ በሪጅኑ ቢሮ አካሂደዋል፡፡

በስብሰባው ላይ እንደተነሳው በዲስትሪክቶቹ በሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚታየው የአቅም ውስንነት ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል፡፡

የኃይል ጭነት ከሚበዛባቸው መስመሮች መካከል የተወሰኑትን ወደ ሌሎች ማከፋፈያ ጣቢያዎች የማዘዋወር ሥራ ትኩረት እንዲሰጠውም መክረዋል፡፡

በአንፎ – ጦር ኃይሎች፣ በኮልፌ – አዲስ ዌስት፣ በጎፋ፣ እና በካራቆሬ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ያለውን የኃይል ጭነት መቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል፡፡

በቀረበው ምክረ ሀሳብ መሰረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኮልፌ ማከፋፈያ ጣቢያ ወደ ጥቁር አንበሳ ማከፋፈያ ጣቢያና ወደ ሸጎሌ ማከፋፈያ ጣቢያ፣ ከአንፎ ማከፋፈያ ጣቢያ ወደ ኮልፌ ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲሁም ከቃሊቲ 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ወደ ኮዬ አቦ የተወሰኑ መስመሮችን የማዘዋወር ሥራ እንዲሰራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ደግሞ ከሰበታ 1 ወደ ረጲ በተዘረጋው 132 ኪሎ ቮልት መስመር ላይ ያለውን የኮንዳክተር መርገብ በፍጥነት እንዲስተካከል እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚታየው የሴቲንግ ችግር እንዲያስተካክል ሀሳብ ቀርቧል፡፡

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ ባስተላለፉት መልዕክት የኃይል አቅርቦት ችግሩን የሚፈቱ ተመሳሳይ ውይይቶች በየወሩ እንደሚከናወኑ ገልፀው ለዘመን መለወጫ በዓል የተሰጡ ሥራዎች አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚቀርብ አረጋግጠዋል፡፡

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top