ዛሬ ጳጉሜን 1 የመሻገር ቀን “የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ኃሳብ በመላ አገሪቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡
እለቱን በማስመልከት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ኢትዮጵያ የተለያዩ ጫናዎችን ተቋቁማ ለስኬት ያበቃችው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ የመሻገር ዘመን ማብሰሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተወሰደ ፈጣን የማሻሻያ ርምጃ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሁን ላይ ግድቡ ከአንድ ሺ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል ብለዋል።
ከለውጡ በፊት ግድቡ በውድቀት አፋፍ ላይ እንደነበር ገልጸው በግድቡ ላይ የተሰራው የማሻሻያ ሥራ እንደ ሀገር ፈተናዎችን ተቋቁሞ ወደ ስኬት ማማ መውጣት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ጫና እንደነበረ ያስታወሱት ኢንጅነር አሸብር የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ፈተናዎችን በጋራ በማሰለፍ ወደ ብልፅግና ማማ የወጡበት የታሪክ እጥፋት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢንጂነር አሸብር የሕዳሴው ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘቡን እውቀቱንና ጉልበቱን ያፈሰሰበት አንጡራ ኃብት በመሆኑ የግድቡ ስኬት በሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ መድገም እንደሚገባ ተናግረዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
