በኢትዮጵያ እና በታንዛኒያ መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን በቅርቡ ሥምምነት እንደሚፈረም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማርኬቲንግና ቢዝነስ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ህይወት እሸቱ እንደገለፁት ከኢትዮጵያ፣ ኬኒያ እና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የሦስትዮሽ ውይይት በናይኖቢ አካሂደዋል።
ውይይቱም በኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የህግ ማዕቀፎች፣ የኃይል ሽያጭ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እና በታንዛኒያ መካከል የኃይል ሽያጭ ሥምምነት ለማድረግ ተደጋጋሚ ድርድሮች ሲካሔዱ መቆየታቸውን ነው አቶ ህይወት ያስታወሱት።
በኬኒያ በተደረገው የሦስትዮሽ ውይይት በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከሥምምነት መደረሱን የገለፁት ዳይሬክተሩ አንድ የማጠቃለያ ውይይት ከተደረገ በኋላ የፊርማ ሥምምነቱ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ህይወት ገለፃ ለታንዛኒያ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እየተካሔደ ያለው ድርድር የኬኒያን ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በመጠቀም የሚከናወን በመሆኑ ከባለፉት የኃይል ሽያጭ ሥምምነቶች ለየት ያደርገዋል።
ከኃይል ሽያጭ ድርድሩ ጎን ለጎን በኬኒያው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኩባንያ (ኬትራኮ) እና በታንዛኒያው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ኩባንያ (ታኒስኮ) መካከል የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኪራይ ሥምምነት ለማካሄድ ውይይቶች በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የኃይል ሽያጭ እና የማስተላለፊያ መስመር ኪራይን አስመልክቶ በሦስቱ ሀገራት መካከል ሥምምነት (EKT Interconnection Agreement ) መፈፀሙን የጠቀሱት አቶ ህይወት ሥምምነቶቹ ወደፊት ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እንደሚያግዝም አስታውቀዋል።
የኬኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኩባንያ (ኬትራኮ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ኢንጂነር ጆን ማቲቮ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንደገለፁት የሦስቱ ሀገራት ውይይት ቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስሩን እውን ለማድረግ ማሳያ ነው።
ከሦስቱ ሀገራት የተውጣጡት ባለሙያዎች በኬኒያ ድንበር ላይ የሚገኘውን የኢስኒያን ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን ጎብኝተዋል።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ቀጣይ ለሚደረገው የኃይል ሽያጭ ሥምምነት ዝግጁ መሆኑንም በጉብኝቱ ወቅት መታዘባቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮ- ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሥምምነት የሚፈረም ከሆነ የኬኒያን ግሪድ በመጠቀም የኢትዮ-ኬኒያ- ታንዛኒያ የኃይል ትስስር እንደሚፈጠር ይጠበቃል።