የበቆጂ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ላይ አጋጥሞ የነበረው ከባድ የዐለት ክምችት የቁፋሮ ሥራውን ፈታኝ ቢያደርገውም በስኬት እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለፀ፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የራስ ኃይል ኮንስትራክሽን መምሪያ የበቆጂ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የሳይት አስተባባሪ አቶ እንዳልካቸው ጃምቦ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በሚገነባበት ቦታ ላይ ከባድ የዐለት ንጣፍ እንዲሁም ጥቁር አፈር መኖሩ የቁፋሮ ሥራውን አስቸጋሪና ጊዜ እንዲወስድ አድርጎታል።
ፕሮጀክቱን ከተያዘለት የ12 ወራት ጊዜ ቀደም ብሎ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ ወደ ሳይት ቢገባም በጣቢያው ላይ ያጋጠመው ከባድ የዐለት ክምችት ግን ከተገመተው በላይ ፈታኝ እንደነበር አስተባባሪው አንስተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አስቸጋሪ የሆኑ የቁፋሮ ሥራዎች እየተገባደዱ መሆኑን የገለፁት አቶ እንዳልካቸው ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የታየው ቁርጠኝነት እና የቡድን ሥራ የተቋሙን እምቅ አቅምና ጥንካሬ ያሳየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ሲቪል መሀንዲስ ሱራፌል ሲያምረኝ በበኩሉ ፕሮጀክቱን ለመገንባት የመሬት ጥናትና የአፈር ምርመራ ሲደረግ በቀላሉ ሊወጣ የሚችል የድንጋይ ክምችት መኖሩ ይታወቅ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ይሁንና የቁፋሮ ሥራው ሲጀመር ከሚገመተው በላይ የሆነና እስከ 3 ሜትር ስፋት ያለው ግዙፍ የዐለት ክምችት በማጋጠሙ የቁፋሮ ሥራው አስቸጋሪ እንዲሆን እንዳደረገው ጠቅሰዋል።
የሲቪልና ኤሌክትሮ መካኒካል ዕቃዎች መትከያ መሠረት ለማውጣት 1 ነጥብ 4 ሜትር ድረስ የሚቆፈር ቢሆንም የድንጋዩ ጥልቀት ከዚያ በላይ በመሆኑ ሳቢያ መልሶ ለመሙላት እና መሰረት ለማውጣት እልህ አስጨራሽ ጉልበት መጠየቁን ገልፀዋል፡፡
የጣቢያው የመቆጣጠሪያ ክፍልና ስዊች ያርድ በሚያርፉበት ቦታ ላይ ጥልቀት ያለው ጥቁር አፈር ማጋጠሙ ሌላው ፈታኝ ችግር እንደነበርም ነው መሀንዲሱ የገለፁት፡፡
ጥቁር አፈር በባህሪው ክብደት የመሸከም አቅም እንደሌለው የገለፁት አቶ ሱራፌል ጥቁር አፈሩን ሙሉ በሙሉ በማንሳትና መልሶ በጠቅጠቅ የመሰረት ማውጣት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ የኤክስካቫተር ሾፌር የሆነው ወጣት ዳግም ደገፋ በ12 ዓመት የአገልግሎት ዘመኑ እንደ አሁኑ ያለ አስቸጋሪ የቁፋሮ ሥራ ገጥሞት እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡
የዐለት ንጣፉ የተያያዘና በጣም ከባድ በመሆኑ በተደጋጋሚ የማሽን ብልሽት እንዳጋጠመው የገለፀው የኤክስካቫተር ሾፌሩ ድንጋዩን ወደ ሌላ ቦታ ለመግፋት በአንድ ማሽን ጉልበት የማይቻል እንደነበር አንስቷል፡፡
በፕሮጀክቱ ትልቅ የቡድን ስሜት መኖሩ ችግሮችን በጋራ ለማለፍ እንዳስቻላቸው የፕሮጀክቱ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ገልፀዋል::