ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ የተለያዩ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መብራቱ ተሾመ ፕሮጀክቱ ስላለፈበት ሂደትና አሁን ስለደረሰበት ደረጃ ገለፃ አድርገዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ዋና ግድብ ግንባታ ከመሬት ወለል 74 ሜትር ከፍታ ላይ መድረሱንና ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑን፣ የትርፍ ውሃ ማስተንፈሻ ቦይ ወይም ስፒል ዌይ ግንባታ 11 በመቶ መከናወኑን፣ የኃይል ማመንጫ ቤት የሲቪል ግንባታም 55 ነጥብ 6 በመቶ ላይ እንደሚገኝ፣ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 62 በመቶ መድረሱን ገልፀውላቸዋል፡፡
የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ከ4 ሺህ 5 መቶ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
በአፍሪካ በግዙፍነቱ ሦስተኛ ደረጃ የያዘው የኮይሻ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ያለበት ደረጃ አበረታች መሆኑን አመራሮቹ በጉብኝታቸው ገልፀዋል።
የኮይሻ ግድብ በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅምና የመልማት ዕድል የሚፈጥር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል።