የኢትዮጵያ የኢነርጂ ዕድገት በጋራ ማደግ መርህ ላይ የተመሰረተ ነው _ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ የኢነርጂ ዕድገት በጋራ ማደግ መርህ ላይ የተመሰረተ ነው _ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ የኢነርጂ ዕድገት ጎረቤት ሀገራትን የሚጎዳ ሳይሆን በጋራ የማደግ መርህ ላይ የተመሠረተ መሆኑን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒሰትር  ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍን በመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ  የምትገነባው የአረንጓዴ ኢነርጂ አካባቢን የማይጎዳ እና ለመላው አፍሪካ የመጣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ብስራት ነው።

ከ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ የኤሌክትሪክ  ኃይል ዕድገትን  ያረጋገጡ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቢያመጡም በነበረው የኢነርጂ አመራረት ችግር ምክንያት በተፈጥሮ ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ዕድገት እንደነበራቸው አንስተዋል።

በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲመጣ ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ ንጹህ ኢነርጂ ማምረት እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል።

ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፍሪካ ግርማ ሞገስና የመቻል ተምሳሌት መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ህዝቦች ከፈለጉና ከወደዱ እንዲሁም ከተደመሩ ግዙፍ ሥራ ጀምረው መጨረስ እንደሚችሉ ያሳየ የንፁህ ኢነርጂ ፕሮጀክት ነው ብለዋል ።

ግድቡ በኢትዮጵያውያን ታስቦ በኢትዮጵያውያን ሀብት ብቻ የተገነባ ለመላው አፍሪካ የምሳሌነት ምልክት እንደሆነም ነው የገለጹት  ።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ የታዳሽ ኃይል ምንጮች የምትገነባቸው ፕሮጀክቶች የወደፊቱን የአፍሪካ ዘመን ዕድገት ለማረጋገጥ አብዛኛው በንጹህ ኢነርጂ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸው የንጹህ ኢነርጂ ኢንቨስትመንቶች ኮፕ 2032 በኢትዮጵያ እንዲዘጋጅና ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ መታሰቡ በአረንጓዴ አሻራ እና በአካባቢ ደህንነት በምትከተለው ፖሊሲ የተገኘ ውጤት መሆኑን አመልክተዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top