ከማከፋፈያ ጣቢያው የሚፈልገውን ኃይል እያገኘ መሆኑን ፋብሪካው ገለፀ

ከማከፋፈያ ጣቢያው የሚፈልገውን ኃይል እያገኘ መሆኑን ፋብሪካው ገለፀ

ከኮምቦልቻ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያ ለምርት ሂደቱ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኘ መሆኑን የአማር ቁጥር አንድ የከረጢትና ፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ አስታወቀ፡፡

የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ እንየው ጌትነት (ዶ/ር) እንደተናገሩት ፋብሪካው የፕላስቲክና የአግሮ ባግ ከረጢቶችን እያመረተ ይገኛል፡፡

እንየው ጌትነት (ዶ/ር)

ፋብሪካው ለብቻው በተዘረጋለት መስመር በቀጥታ ከማከፋፈያ ጣቢያው የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኘ መሆኑን በመግለጽ አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንደተቀረፈ ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል የሚያጋጥመው የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ከፍተኛ የምርት ብክነት እንዲያጋጥም የሚያደርግ በመሆኑ በፋብሪካዎች ውጤታማነትና ትርፋማነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል ብለዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በጣቢያው ላይ ለሚከናወኑ የተለያዩ ሥራዎች ኃይል ለማቋረጥ ሲታቀድ ለፋብሪካው ከ24 ሰዓት በፊት ስለሚያሳውቅ በምርት ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ብክነቶችን ቀድሞ የመከላከል ሥራ ይከናወናል፡፡

ፋብሪካው አሁን ላይ ለምርት ሂደቱ የሚያስፈልገውን አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኘ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ይህም ፋብሪካው የምርት ሂደቱን እንዲያሳድግ ከማገዙም ባለፈ በየጊዜው ማስፋፊያ በማድረግ ተጨማሪ አዳዲስ ማሽነሪዎችን እንዲያስገባ ዕድል ፈጥሮለታል ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ።

በማከፋፈያ ጣቢያው ላይ የሚከናወኑ የማስፋፊያ ሥራዎች የፋብሪካውን የኃይል አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዳሳደገው ጠቅሰው ፋብሪካው በተያዘው ዓመት አዳዲስ ማሽነሪዎችን በማስገባት ተጨማሪ ኃይል የሚጠቀምበትን አጋጣሚ መፍጠሩንም አንስተዋል፡፡

አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መኖር አዳዲስ ኢነቨስትመንቶችን ለመጀመር፣ ለከተሞች ዕድገት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና አለው ያሉት እንየው (ዶ/ር) ያለውን የኃይል አቅርቦት ተከትሎ ፋብሪካው በቅርቡ ተጨማሪ ማሽነሪዎችን በማስገባት የሲሚንቶ ከረጢት ለማምረት አቅዶ እየሰራ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ፋብሪካው አሁን ላይ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና በምርቶቹም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከማከፋፈያ ጣቢያው ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት መኖሩን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ግንኙነቱ የምርት ብክነትን በማስቀረጥ ምርታማነትን ለማሳደግ እና በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ በጋራ በመወያየት የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡

በፋብሪካው የኤሌክትሪክ ክፍል ኃላፊ አቶ ወርቁ ደረሰ በበኩላቸው ፋብሪካው ከማህበረሰቡ ጋር ኃይል ሲያገኝ በነበረበት ጊዜ የቮልቴጅ መዋዠቅ በመኖሩ በምርት ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበረው አስታውሰዋል፡፡

ይሁንና ፋብሪካው በቀጥታ ከማከፋፈያ ጣቢያው ኃይል ማግኘት ከጀመረ ወዲህ የኃይል መቆራረጥ በመቀነሱ በምርት ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ፋብሪካው አስተማማኝ ኃይል እያገኘ መሆኑን በመጠቆም በቀጣይ ለሚደረጉ ማስፋፊያዎች ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚቀርብ ከጣቢያው ይሁንታ መገኘቱንና ለዚህም ፋብሪካው ትራንስፎርመር ዝግጁ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top