በኢትዮጵያ በመንግስት እና የግል አጋርነት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ሊገነቡ ነው

በኢትዮጵያ በመንግስት እና የግል አጋርነት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ሊገነቡ ነው

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥትና የግል አጋርነት ዘርፍ (Public- Private Partnership) የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታ ሊከናወን ነው።

‎የኢትዮጵያ መንግስት ከዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ጋር ሁለት የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ለመገንባት የ400 ሚሊዮን ዶላር ሥምምነት ተፈራርሟል።

‎ሥምምነቱ 198 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሁርሶ- አይሻ ባለ 400 ኪሎ ቮልት እና 206 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን የደገሃቡር- ቀብሪድሃር ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ለመገንባት ያለመ ነው።

ፕሮጀክቶቹን ግሪድዎርክስ (Gridworks) የተሰኘ በዩናይትድ ኪንግደም የልማት ፋይናንስ የሚደገፍና በአፍሪካ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሳተፍ ኩባንያ እንደሚገነባ በፊርማ ሥነስርዓቱ ላይ ተጠቅሷል።

ግንባታዎቹ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ከአዳዲስ የኃይል ምንጮች የሚመረተውን ኃይል ወደ ግሪድ ለማስገባት ያግዛሉ ተብሏል።

የፕሮጀክቶቹ መገንባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ለመጣው የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ለመጨመር እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ተመላክቷል።

ፕሮጀክቶቹ የሀገሪቱን ብሔራዊ የልማት ዕቅድ የሚደግፉ እና በአነስተኛ ዋጋ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪዎችና ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የሚረዱ መሆናቸውም ነው የተገለፀው።

የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቶቹ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለኑሮ መሻሻል መሠረታዊ ጉዳዮች እንደሆኑም ተጠቅሷል።

ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ሀገራትን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር የሚረዱ ከመሆናቸውም በላይ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ድርሻቸው የጎላ መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቶቹ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥት እና የግል አጋርነት ማዕቀፍ የሚገነቡ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በመሆናቸው ወደ ዘርፉ የግል ባለሀብቶችን ለመሳብ መንገድ ከፋች ይሆናሉ ተብሏል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top