የኮምቦልቻ ቁጥር 1 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እና በአካባቢው ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች መመስረት እንዲሁም ለሥራ ዕድል ፈጠራ መሰረት የጣለ መሆኑን የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ተናገሩ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ሙስጠፋ ጀማል እንደተናገሩት ማከፋፈያ ጣቢያው ለፋብሪካው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ በመገንባቱ ፋብሪካው እና ማከፋፈያ ጣቢያዉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡

ፋብሪካዉ በተለያየ ጊዜያት የማስፋፊያ ሥራ ባከናወነበት ወቅት የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከጣቢያው ሲያገኝ መቆየቱን በመጠቆም አሁን ላይም 6 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት ኃይል እየተጠቀመ እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
ፋብሪካው ለአካባቢውና ለሀገር ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለውን ሚና በመረዳት የማከፋፈያ ጣቢያው የሥራ ኃላፊና ሠራተኞች የኃይል ማነስና መቆራረጥ በፋብሪካዉ ላይ የሚያደርሰውን ኪሳራ በመገንዘብ ችግሮች ከመድረሳቸው አስቀድሞ የመፍትሔ እርምጃዎችን እየወሰዱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡


በመስመሩ ላይ የሚያጋጥመውን የቮልቴጅ መዋዠቅና የኃይል መቆራረጥ ችግሮችን በጋራ በመነጋገር እና በትብብር በመስራት መፍትሔ እየተሰጠ በመሆኑ የቮልቴጅ መዋዠቁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻል መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ሙስጠፋ ገለፃ በነባር ጣቢያዎች ላይ የሚከናወኑ የማሻሻያ ሥራዎች እና በኮምቦልቻ ከተማ እየተገነባ ያለው አዲስ የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ የፋብሪካውን የኃይል ፍላጎት በማሳደግ ተጨማሪ ማሽነሪዎችን እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባትና ምርታማነትን ለመጨመር መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራል፡፡
ፋብሪካው የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ በማምጣት እና የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በማስቀረት ለሀገሪቱ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢንዱስትሪዎች መመስረት፣ ለከተሞች መስፋፋት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ መሰረት መሆኑን በማንሳት የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለመመስረቱና አሁን ለደረሰበት ደረጃም የማከፋፈያ ጣቢያው የኃይል አቅርቦት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ነው ሥራ አስኪያጁ ምስክርነታቸውን የሰጡት፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


