ተቋሙ የኒውክሌር ኮሚሽንን ለማጠናከር የሚያስችል ድጋፍ እያደረገ ነው

ተቋሙ የኒውክሌር ኮሚሽንን ለማጠናከር የሚያስችል ድጋፍ እያደረገ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባውን የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን ለማጠናከር የሚያስችል የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን በተቋሙ የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ገለፀ፡፡

የዘርፉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ እንደገለፁት ኮሚሽኑ የሚያከናዉነው ሥራ እንደ ሀገር ብሎም ተቋም ያለውን የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ለሚያከናውነው ሥራ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት በመንግስት አቅጣጫ መሰጠቱን ያነሱት አቶ ደመረ ይህን ተከትሎም ተቋሙ ለኮሚሽኑ ሥራ መነሻ የሚሆን የዓይነትና የገንዘብ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

ተቋሙ ምንም እንኳን ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን እየመራና እያስተዳደረ የሚገኝ ቢሆንም በቀጣይ የሚገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ የፋይናንስ አቅሙን ባገናዘበ መልኩ የግማሽ ቢሊየን ብር እና ከ67 ነጥብ 21 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገዙ ሁለት ዘመናዊ ተሸከርካሪዎችን ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

የገንዘብ ድጋፉ ከዚህ በፊት ለኮሚሽኑ የተሰጠ ሲሆን ተሸከርካሪዎችን ደግሞ በትላንትናው ዕለት ማስረከብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

እንደ አቶ ደመረ ገለፃ ተቋሙ የፋይናንስ ችግሩን ተቋቁሞ ለኮሚሽኑ ያደረገው ድጋፍ ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች በማሳለጥ የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት ባለፈ እንደ ሀገር ያለውን የኢነርጅ ፍላጎት ለማሟላት ያግዛል፡፡

በቀጣይ ተቋሙ የፋይናንስ አቅሙን መሰረት ባደረገ መልኩ ለኮሚሽኑ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው አረጋግጠዋል።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጷጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምርቃ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ የህዳሴን ግድብ የሚተካከል ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የሚውል የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ በቅርቡ ሥራ ትጀምራለች” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ዕቅዱን ለማሳካትም ከሩሲያ ጋር ከተደረገው የኒውክሌር ኃይል የድርጊት መርሃ ግብር ስምምነት በተጨማሪ ከኒውክሌር ኃይል የማመንጫ ሥራ የዓለም አቀፍ የህግ እና የቁጥጥር ማዕቀፎችን በተከተለ መልኩ እንዲፈፀም ለማድረግ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top