በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች እና በዙሪያቸው ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምስራቅ 1 ሪጅን አስታወቀ፡፡
የሪጂኑ ዳይሬክተር አቶ በድሩ አህመድ እንደተናገሩት በሪጅኑ ውስጥ አምስት ባለ 132 እና ሦስት የባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዲሁም የተለያየ የኪሎ ቮልት መጠን ያላቸው 973 ነጥብ 68 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመሮች ይገኛሉ፡፡
በሪጅኑ በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች እና አካባቢያቸው ያለው የኃይል ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ከአካባቢው የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ከከተሞች ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ለመመለስ ባለፉት ስድስት ወራት በኮምቦልቻ ቁጥር 1 እና 2 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግና ማስፋፊያ፣ የመቆጣጠሪያ ብሬከር የማዘመን እንዲሁም ደንበኞችን ከአንዱ ጣቢያ ወደ ሌላ ጣቢያ በማዘዋወር የኃይል ጭነት የማመጣጠን ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ በድሩ አስረድተዋል፡፡
በጣቢያው ላይ ለሚቀርቡ የኃይል ፍላጎት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ ትራንስፎርመር ለማስቀመጥ ዕቅድ መያዙንም አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም በኮምቦልቻ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ተጨማሪ ትራንስፎርመር በመትከል ከኮምቦልቻ ቁጥር 1 የተወሰኑ ደንበኞችን ወደ ቁጥር 2 በማዛወር በጣቢያው ላይ የነበረውን የኃይል ጭነት ማቃለል እንደተቻለ ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡
በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ እየተከናወነ ካለው የአቅም ማሳደግ፣ ማስፋፊያና ማዘመን ሥራዎች በተጨማሪ በአካባቢው በፍጥነት እያደገ ያለውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ተቋሙ በኮምቦልቻ እና ደሴ ከተሞች ላይ አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እየገነባ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ሲጠናቀቁ ሪጂኑ ለከተሞቹ እና አካባቢው ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ዕድል እንደሚፈጥሩም አቶ በድሩ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ሪጂን ዳይሬክተር አቶ ሀብቱ አበበ በበኩላቸው በደሴና ከምቦልቻ ከተሞች እና አካባቢው ባለው የኢንዱስትሪ መስፋፋት ምክንያት የኃይል ፍላጎቱና አቅርቦቱ የተመጣጠነ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡


የሰሜን ምስራቅ 1 ሪጅን የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎችን ለመመለስ በአካባቢው በሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል በኮምቦልቻ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የተከናወነው የአቅም ማሳደግና ማስፋፊያ እንዲሁም ከአንዱ ጣቢያ ወደ ሌላ ጣቢያ የተደረገው ደንበኞችን የማዘዋወር ሥራ ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ በአገልግሎቱ ላይ ሲነሱ የነበሩ በርካታ ችግሮች እንዲቃለሉ ማድረጉን አቶ ሀብቱ አስረድተዋል፡፡
ደንበኛ የማዘዋወር ሥራው የደሴ ከተማን የፈረቃ የኃይል አቅርቦት እንዲያጥር ማስቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች እየተገነቡ የሚገኙ የማከፋፈያ ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ አገልግሎቱ በከተሞችና በዙሪያው ለሚገኙ ወረዳዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እያከናወነ ያለውን ሥራ እንደሚደግፉም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ለማህበረሰቡ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ሁለቱ ተቋማት በትብብር እየሰሩ ስለመሆኑም የሥራ ኃላፊዎቹ አመልክተዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


