የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት ስድስት ወራት በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች ክርክር ካካሄደባቸው የፍትሀብሔርና የሥራ ክርክር መዝገቦች ከ806 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ገለፀ፡፡
በተቋሙ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም በቀለ እንደገለፁት በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በተቋሙ ውስጥ ግልጽ እና ወጥ የአሰራር ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ እንዲሁም ክስ የመርታት አቅምን በማሳደግ የተቋሙን ጥቅም ለማስጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ደረጃ ላይ የሚገኙ 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የገንዘብ መጠን ያላቸው 244 የፍትሀብሔር መዝገቦች ላይ ክትትል ሲደረግ መቆየቱንና 73 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በበጀት ዓመቱ 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን የብር መጠን ያላቸው 32 የሥራ ክርክር መዝገቦች ላይ ክትትል ተደርጎ በ8 መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሮ ጋር በቅንጅት በመስራት 654 ነጥብ 14 ሚሊዮን ብር መጠን ያላቸውን 19 መዝገቦች ሙሉ ለሙሉ ለተቋም እንዲወሰን መደረጉን አብራርተዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ውሳኔ ከተሰጠባቸው የፍትሀብሔር እና የሥራ ክርክር መዝገቦች በድምሩ 806 ነጥብ 62 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ወ/ሮ መስከረም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በ114 የወንጀል መዝገቦች ላይ ክትትል ሲደረግ መቆየቱንና ከዚህ ውስጥ በ3 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መተላለፉንም ጠቁመዋል፡፡
ከ1 ነጥብ 92 ብሊዮን ብር በላይ መጠን ያላቸው 5 የግብር እና ታክስ ውሳኔ ላይ ቅሬታ ቀርቦ በክርክር ሂደት ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ ከካሳ ጋር ተያይዞ ያሉና ከ3 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር በላይ መጠን ያላቸው 6 የክስ መዝገቦችን ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ መምሪያው በ238 ጉዳዮች ላይ የሕግ አስተያየት እና ምክር መሰጠቱንም አንስተዋል፡፡
በሕግ አገልግሎት መምሪያው የሚሰጡ የሕግ አስተያየቶች፣ የመዝገብ ክርክር ሂደቶች እና ሌሎች የአሠራር ሂደቶችን ጥንካሬና ክፍተቶች በመለየት የመፍትሔ ምክረ-ሐሳብ የሚያቀርብ ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ እንዲሁም በሕብረት ሥምምነት ላይ በ10 ዙር ለ202 ሥራ መሪዎች ሥልጠና መሰጠቱን ያስታወሱት ወ/ሮ መስከረም የክርክር መዝገብ አያያዝ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የመዝገቦች ፍሰት መከታተያ መተግበሪያ እንዲበለጽግ መደረጉንም ጠቁመዋል።
የመዝገብ ክርክርም ሆነ የሕግ ምክርና አስተያየት በጋራ ውይይት መሰጠቱ፣ ከተለያዩ የፍትህ አካላት ጋር በጥምረት መስራቱ እና ለሁሉም ክፍሎች ተደራሽ ለመሆን ጥረት መደረጉ እንዲሁም የመዝገቦች ፍሰት መከታተያ ሶፍትዌር መበልጸጉ በበጀት ዓመቱ በጥንካሬ መገምገሙን አንስተዋል፡፡
የካሳ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ባለመውጣቱና ክልሎች ወደ ትግበራ አለመግባታቸው፣ የመሬት ግብርና ሊዝ ክፍያ ጥያቄ ከፍተኛ መሆኑ፣ ለሕግ ባለሞያዎች ሥልጠና የሚሰጡ አካላትን ማግኘት አለመቻሉ፣ የሕግ አስተያየት ጠያቂ ክፍሎች ማሟላት ያለባቸውን ሰነዶች በወቅቱ አለሟሟላትና ሕጉ ከሚለው ይልቅ የራስ ፍላጎት ብቻ እንዲታይ መፈለግ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
መምሪያው ቅንጅታዊ አሰራሩን በማጎልበትና የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ እንዲሁም የነበሩ ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብና የተቋሙን ጥቅም ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራ ወ/ሮ መስከረም ገልጸዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”