የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቀጣናዊ የኃይል ትስስሩን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት ከሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ጋር በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ለመተሳሰር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር
ከደቡብ ሱዳን ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን ሥምምነት ከሦስት ዓመታት በፊት የተፈረመ ሲሆን በሁለቱም ወገን ሂደቱን የሚከታተል የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡድኑ ከየትኛው ጣቢያ ወደ ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሄድ ማድረግ ይቻላል? የመሠረተ ልማት ግንባታው ምን ያህል ኪሎ ሜትር ይሆናል? ፕሮጀክቱ ምን ያህል ወጪ ይፈልጋል? የሚሉና ሌሎች ዝርዝር ሥራዎችን እንደሚያከናውን አስረድተዋል፡፡
የባለሙያዎቹ ቡድን እያከናወነ ባለው ሥራ ከሚገኘው ውጤት በመነሳት ውሳኔ እንደሚሰጥበት አብራርተዋል።
የባለሙያዎቹ ቡድን ጥናት በጋራ የሚቀርብ መሆኑንና ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው ፋይናንስ እየተከናወነ ባለው ጥናት እንደሚመለስም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ጅቡቲና እና ኬኒያ በተጨማሪ ለታንዛኒያ ኃይል እያቀረበች እንደምትገኝ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ምርቃት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቀጠናው በትብብር በመሥራት፣ ከልማት መቋደስና አብሮ ማደግ ከተቻለ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የአፍሪካ ዘመን መሆኑንና ኢትዮጵያም ለዚህ ፈር ቀዳጅ ሀገር መሆኗን መግለጻቸው ይታወሳል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”