በሲዳማ ክልል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ከስርቆት ለመከላከል በየደረጃው ከሚገኙ የመስተዳድር አካላት እና ከተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎች ጋር በይርጋለም ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ አንድ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ንጉሴ ስለ ተቋሙ አጠቃላይ ታሪካዊ ዳራ እና ሪጅኑ እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራት ገለፃ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2022 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሀገራዊና ክፍለ አህጉራዊ የኃይል ፍላጎትን ሊሸከም የሚችልና ተመራጭ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ተቋም ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ፍላጎትን ለሟሟላት ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ የተደረገባቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች የተገነቡ ቢሆንም ማህበረሰቡ መሰረተ ልማቶችን በእኔነት ስሜት ባለመጠበቁ ለጉዳት እየተጋለጡ እንደሚገኙ ነው የገለፁት፡፡



በዚህም በሀገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ውድመት እንዲደርስ ከማድረጉም ባለፈ ለማህበረሰቡ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ በሚከናወነው ሥራ ላይ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
በሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞሲሳ ገልቻ በበኩላቸው በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ በየትኛው ቀበሌና አካባቢ ስርቆት በስፋት እንደተፈጸመ፣ በየቀበሌዎቹ በምን ያህል ምሰሶዎች ላይ እንደተፈፀመ፣ ምን ያህል የምሰሶ አካላት እንደተወሰዱ እና ምን ያህል ምሰሶዎች እንደወደቁ እንዲሁም በብር ሲሰላ ምን ያህል ኪሳራ እንደደረሰ የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል፡፡
በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን ለመከላከል የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና ማህበረሰቡ በቅንጅት በመስራት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም የሥራ ኃላፊዎቹ አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ አንድ ሪጅን የሥራ ኃላፊዎች፣ በሲዳማ ክልል በየደረጃው የሚገኙ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የቀበሌ እና የከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች ማኀበት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


