ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲሰማሩ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል

ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲሰማሩ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የተቀላቀሉ አዳዲስ ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲሰማሩ ሙያዊ ሥነ- ምግባርን ባከበረ መልኩ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው በተቋሙ የሰው ሀብት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ አበበ አሳሰቡ፡፡

የኢትዮ ፓወር አካዳሚ ተቋሙን ለተቀላቀሉ አዳዲስ ሠራተኞች ባዘጋጀው የሥራ ላይ ትውውቅ ስልጠና ማስጀመሪያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ እንደተናገሩት ስልጠናው ስለ ተቋሙ አጠቃላይ ገጽታ እና ሠራተኞች ወደ ፊት ስለሚያከናውኗቸው ሥራዎች ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሠራተኞች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ልምድ ወደ ተግባር በሚለውጡበት እና ከተቋሙ ተልዕኮ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው የሥራ ቦታዎች ላይ የሚሰማሩ በመሆናቸው ሁሉም ወደሚመደቡበት የሥራ ቦታ በመሄድ ሀገራዊ አሻራቸውን ማሳረፍ እንደሚኖርባቸውም ነው የገለጹት፡፡

ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት አዳዲስ ተቀጣሪ ሠራተኞች ከፍተኛ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው የተናገሩት አቶ አታላይ ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲሰማሩ ሙያዊ ሥነ- ምግባርን ባከበረ መልኩ ሥራቸውን በማከናወን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

በተቋሙ የኢትዮ ፓወር አካዳሚ የሰው ሀብት ስልጠናና ልማት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምስ ሰይፉ በበኩላቸው ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲሰማሩ የኦፕሬሽን ሥራው በሚከናወንበት የአሰራር ስርዓት ላይ ግንዛቤ በመያዝ ሥራዎችን የአሰራር ስርዓቶችን በተከተለ መልኩ በአግባቡ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ለሁለት ሳምንት የሚቆየው ስልጠና በተቋሙ አጠቃላይ ገጽታ፣ ሠራተኞች ከተቋሙ ስለሚያገኟቸው አገልግሎቶችና ጥቅማ ጥቅሞች፣ በተቋሙ ቆይታቸው ስለሚኖራቸው ሚናና ስለሚጠበቅባቸው ኃላፊነት፣ የሥራ እና ሙያዊ ስነ-ምግባር እንዲሁም የሥራ ላይ ጤናና ደህንነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በተጨማሪም በኤሌክትሪክ ኃይል እና በኃይል ማመንጫዎች መሰረታዊ የአሰራር ሥርዓት፤ የሜካኒካል እና የኤሌክትሪካል ሥርዓቶች በኃይል ማመንጫዎች ውስጥ ስለሚኖራቸው ሚና እንዲሁም ስለማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች አጠቃላይ የአሠራር ደረጃዎች እና ሂደቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ከስልጠናው መርሃ ግብር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top