በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት የፈጸሙ አካላት በእስራት ተቀጡ

በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት የፈጸሙ አካላት በእስራት ተቀጡ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት የፈጸሙ ወንጀለኞች በእስራት መቀጣታቸውን የተቋሙ የሕግ አገልግሎት መምሪያ አስታወቀ፡፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም በቀለ እንዳስታወቁት ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ከ107 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የመቱ – ማሻ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት 100 ሜትር ርዝመት ያለው የኮንዳክተር ገመድ ላይ የስርቆት ወንጀል ተፈፅሟል፡፡

ወ/ሮ መስከረም በቀለ
የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዳይሬክተር

የስርቆት ወንጀሉን በመፈጸም የተጠረጠሩት በማሻ ወረዳ ቄጃ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጋሻው ዝናው እና አቶ ይርጋለም አዲኖ የተባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ አንደኛው ተከሳሽ የኮንዳክተር ገመዱን በመቁረጥ በሁለተኛ ተከሳሽ ባጃጅ ላይ በመጫን ከቦታው ለማሸሽ ሲሞክሩ በአካባቢው የፀጥታ አካላትና በሕብረተሰቡ ትብብር እጅ ከፈንጅ መያዛቸውን አብራርተዋል፡፡

መምሪያው ከደቡብ ምዕራብ ሪጅን እና ከተቋሙ የመሰረተ ልማት ደህንነት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ስርቆቱን በፈጸሙ ወንጀለኞች ላይ ክስ እንዲመሰረት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ መስከረም ገለፃ የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም የሻካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት የቴሌኮሙኒኬሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል አውታሮችን ደህንነት ለመጠበቅ የወጣ አዋጅ ቁጥር 464/1997 ዓ.ም በመተላለፍ ተጠርጣሪዎቹ ጥፋተኛ ተብለው በዚሁ አዋጅ በአንቀጽ 4 ላይ የተቀመጠውን የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

በዚህም በአንደኛ ተከሳሽ አቶ ጋሻው ዝናው ላይ በአምስት ዓመት እንዲሁም በሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ይርጋለም አዲኖ ላይ በስምንት ወራት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል፡፡

የፍትህ አካላት እና ሕብረተሰቡ የኃይል መሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት አመስግነው በቀጣይም ሁሉም ዜጋ በመሰረተ ልማቶቹ ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን በመከላከል ሀገራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top