በሸኽዲ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ባጋጠመ የእሳት አደጋ ምክንያት ኃይል ተቋርጦባቸው የነበሩ የምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢዎች ዳግም ኃይል እንዲያገኙ መደረጉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ተሻገር እንዳስታወቁት በእሳት አደጋው በአንድ የ33 ኪሎ ቮልት ገቢ እና ሦስት የ33 ኪሎ ቮልት የወጪ መስመሮች ላይ የሚገኙ ፓናሎች እና ብሬከሮች ላይ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር።


በተከሰተው አደጋ ለመተማ ዮሐንስ ከተማና አካባቢው ኃይል ተቋርጦ መቆየቱን ያቀርብ ተናግረዋል።
በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ሁኔታ የተነሳ መደበኛ የፍተሻና የክትትል ሥራዎች ሳይከናወኑለት መቆየቱ ለአደጋው መከሰት እንደ አንድ ምክንያት መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡
ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት በሞጣ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የጂ.አይ.ኤስ ስዊችጊር ገጠማ መከናወኑን ተከትሎ የጣቢያውን ነባር ብሬከሮች ወደ ሸኽዲ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በማጓጓዝ ጥገናውን መከናወን መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በጣቢያው የትራንስፎርመር፣ የኬብል እና ሌሎች መለዋወጫዎች ላይ የፍተሻ እና የጥገና ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው በአደጋው ምክንያት የተቃጠሉ የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች በአዲስ የመተካት ሥራ መሰራቱንም ገልፀዋል፡፡
የተቋረጠውን ኃይል ለመመለስ በተደረገ አፋጣኝ የጥገና ሥራ ከጣቢያው ኃይል ሲያገኙ የነበሩ ሁሉም አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ መደረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
እንደ ጌታቸው ገለፃ ወደፊት የጣቢያውን የኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች በዘመናዊ የጂ.አይ.ኤስ (GIS) ቴክኖሎጂ የመተካት ሥራ ለማከናወን ዕቅድ ተይዟል፡፡
ሪጅኑ በሚያስተዳድራቸው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለማድረግ የእሳት ማጥፊያ ሲሊንደሮችን የመሙላት እና በየጣቢያው የማሰራጨት ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ነው ያብራሩት፡፡
ያጋጠመው ችግር እስኪፈታ ድረስ በትዕግስት ለጠበቁ ደንበኞች እንዲሁም በጥገና ሥራው ላይ ርብርብ ሲያደርጉ ለነበሩ የጥገና ሠራተኞች በሙሉ ዳይሬክተሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



