የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ለተቀላቀሉ ሠራተኞች በሙያ ደህንነት እና ጤንነት ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እየተሠጠ ይገኛል።
በተቋሙ የሙያ ደህንነት እና ጤንነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኮርሳ ታሬሳ እንደገለፁት ሥልጠናው ተቋሙን የተቀላቀሉ ሠራተኞች ወደ መደበኛ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት በተቋሙ ውስጥ ያለውን የሥራ ከባቢ በውል እንዲገነዘቡ ያለመ ነው፡፡

ሠራተኞቹ በሥራ ላይ ሊያጋጥማቸው የሚችሉ የሙያ ደህንነት ስጋቶችን በመለየት መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማድረግ የታሰበ መሆኑንም ነው የገለፁት።


አንድ ሠራተኛ ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችንና መከላከያ መንገዶችን ማወቁ ከጉዳት ነፃ ሆኖ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ይረዳዋል ብለዋል።
አቶ ኮርሳ እንዳሉት በሥራ ላይ አደጋ ቢከሰት እንኳ ጉዳቱ ሳይሰፋ እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻልና የመጀመሪያ እርዳታ አሰጣጥ መርሆዎችን ሥልጠናው አካቷል፡፡
ይህም ሠራተኞች የራሳቸውን ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ አደጋ በሚያጋጥምበት ወቅት ለሥራ ባልደረቦቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ለማስቻል አቅም እንደሚፈጥርላቸዋው ገልፀዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
