የኢነርጂ ደህንነት የሀገር ደህንነት ጉዳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።
የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በዛሬው ዕለት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቋል፡፡
በዚህ ወቅት ኢንጂነር አሸብር እንደገለጹት ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር የነበረውን 4 ሺህ ሜጋ ዋት ከእጥፍ በላይ በማሳደግ ከ9 ሺህ 700 ሜጋ ዋት በላይ ማድረስ ተችሏል።
ለዚህም የለውጡ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረትና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ድርሻቸው ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ መጠናቀቅ እንደ ሀገር የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል በመሆን ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ለማስተሳሰር የተያዘውን ግብ አመላካች መሆኑን ገልፀዋል።
ከአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ በተጨማሪ 350 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት ለመገንባት እየተሰራ ነው ያሉት ኢንጂነር አሸብር በመንግሥትና በግል አጋርነት 300 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ውል ተፈርሞ ለግንባታ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
በምስራቁ የአይሻ ኮሪደር ከንፋስ እስከ 9 ሺ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም መኖሩንም አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት ለኬኒያ፣ ጅቡቲና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል እየቀረበ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቀጣይ ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ጋር የኃይል ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከ7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱንና የውጭ ምንዛሬ ግኝቱም 247 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ተናግረዋል።
ይህም የአይሻ ሁለት የንፋስ እና የኮይሻ የውሃ የኃይል ማመንጫ ግንባታዎችን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን በፋይናንስ ለመደገፍ እንዳስቻለው ጠቁመዋል።
ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ የኢነርጂ ሴክተሩን በማሳደግ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማማ ለማድረግ ለሚሰጡት ቆራጥ አመራር፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

