በመንግሥት እና የግል አጋርነት ማዕቀፍ ለሚገነባውና 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ላለው የአይሻ 1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የፋይናንስ ሥምምነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከዋና ዋና የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የከፍተኛ ደረጃ የአበዳሪዎች የቅድመ ኢንቨስትመንት ምርመራ ስብሰባ በሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሂዷል፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያዎችን በማድረግ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመንግሥትና የግል አጋርነት በኢነርጂ ዘርፍ የመሠረተ ልማት ፋይናንስ ክፍተትን ለመሙላት እና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ማዕከላዊ የፖሊሲ መሣሪያ ሆኖ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የአይሻ 1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የመንግሥትና የግል አጋርነት የሚለማ የመጀመሪያው የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት በመሆኑ በቀጣይ ለሚሰሩ ሥራዎች እንደ መነሻ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የኃይል አማራጮች ለማስፋት እና የንጹህ ኃይል ምርትን ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ በፕሮጀክቱ የግንባታ እና የሥራ ሂደት ወቅት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮግራም መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጥላዬ መድረኩ ዓለም አቀፍ አበዳሪዎችን፣ የልማት ፋይናንስ ተቋማትን እንዲሁም የፕሮጀክቱን የሕግ፣ የፋይናንስ እና የቴክኒክ አማካሪዎችና ከፍተኛ ኃፊዎች እና ተወካዮችን በአንድ ላይ ያገናኘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


ይህም የፕሮጀክቱን የፋይናንስ ሥምምነት ለማጠናቀቅ በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ የቅድመ ኢንቨስትመንት ምርመራ ሂደት ቁልፍ እርምጃ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪን፣ ከሀገር ውጭ የገንዘብ ዝውውርን እና አግባብነት ያላቸው የቁጥጥር ማዕቀፎችን እንዲሁም የመንግሥት ዋስትና ዝግጅቶችን በተመለከተ ከአበዳሪዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ መስጠታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በመላው አፍሪካ 2 ሺ 600 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶችን በማልማት በኦፕሬሽን ላይ የሚገኙ ሲሆን በጠቅላላው 4 ሺህ 140 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን 20 በሚደርሱ ሀገራት በማልማት ላይ በሚገኘው አሚያ ፓወር (AMEA Power) የሚገነባ መሆኑንና ለግንባታውም 620 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የፋይናንስ ወጪ የሚደረግበት የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአሁኑ ወቅት ከፀሐይ፣ ከንፋስ፣ ከውሃና ከጂኦተርማል እስከ 3 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ 20 የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮጀክቶችን ለይቶ በተለያየ የልማት ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


