በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ባለፉት ስድስት ወራት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች ማከናወኑን አስታወቀ።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ተሻገር እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በዕቅድ ላይ የተመሰረቱ የአስቸኳይ ጥገና እና የፍተሻ ሥራዎች ተሰርተዋል።
በግማሽ በጀት ዓመቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማረጋጋት እና ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የጥገና እና የማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀው ይህም የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ እና የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ለማሟላት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡



ሪጅኑ የኃይል አቅርቦቱን ይበልጥ አስተማማኝና ተደራሽ ለማድረግ በአራት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ማከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
የሞጣ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የዘመናዊ ስዊችጊር ገጠማ ሥራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ በባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ እና አዘዞ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ የአቅም ማሳደግ ሥራዎች አፈፃፀማቸው ከ50 በመቶ በላይ መድረሱንም ነው የተናገሩት፡፡
በስርቆት ምክንያት የወደቁ ስድስት የባህር ዳር – ወልድያ- ኮምቦልቻ ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን በራስ አቅም መልሶ የመጠገን ሥራ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ በአዘዞ – ሸህዲ እና በሞጣ – ደብረ ማርቆስ መስመሮች ላይ በተፈፀመ የስርቆት ወንጀል ምክንያት ወድቀው የነበሩ ስምንት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ተጠግነው ዳግም አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
ከመገጭ የውሃ መስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ጋር ተያይዞ በባህርዳር- አዘዞ የኃይል ማስተላለፊያ አንድ የብረት ምሰሶ ላይ ደርሶ የነበረን ጉዳት መልሶ መጠገን መቻሉንም ነው የገለፁት፡፡
በበለስ – ጃዊ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት ሰባት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች መውደቃቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት ሦስቱን መልሶ የማቆም ሥራ መሰራቱን ጠቅሰው ቀሪዎቹ አራት ምሰሶዎችን ደግሞ በሚቀጥሉት ሳምንታት ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ በትራንስፎርመር ብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁሞ የነበረውን የጃዊ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን ዳግም ከግሪድ ሥርዓቱ ጋር ለማገናኘት የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውንም ነው አቶ ጌታቸው የተናገሩት፡፡
የሰሜን ምዕራብ ሪጅን በስሩ 10 የተለያዩ የኪሎ ቮልት መጠን ያላቸውን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና ከ1 ሺህ 720 ኪሎ ሜትር በላይ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ያስተዳድራል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

