በኮምቦልቻ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ በየጊዜው እያደገ የሚመጠውን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጣቢያው ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡
ኃላፊው አቶ ዝናቡ ገብሩ እንዳስታወቁት የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የኢንዱስትሪ እና ከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ በማከፋፈያ ጣቢያው ላይ ያለው የኃይል አቅርቦት ፍላጎት በፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው በ2002 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት ሲጀምር 63 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመር እና አራት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ብቻ እንደነበሩት ያስታወሱት አቶ ዝናቡ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት መሰረት በማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የአቅም ማሳደግ፣ ማስፋፊያና ማዘመን ሥራዎች እንደተከናወኑለት ተናግረዋል፡፡



በዚህም በ2010 ዓ.ም 63 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለው አንድ ተጨማሪ ትራንስፎርመር በመትከል የ33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮቹን ቁጥር ወደ ስድስት ማሳደግ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
ይሁንና ከጊዜ በኋላ አንዱ የወጭ መስመር ብሬከር ወደ ሰመራ ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲዛወር በመደረጉ ከመስመሩ ኃይል ሲያገኙ የነበሩ ደንበኞች በሌሎች መስመሮች ላይ ተደርበው ኃይል እያገኙ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት 50 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመር በመትከል ተጨማሪ ስድስት ባለ 15 ወጭ መስመሮችን ወደ አገልግሎት ማስገባት በመቻሉ የኃይል አቅርቦቱን ማሳደግ እንደተቻለ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ከአቅም ማሳደግና ማስፋፊያ ሥራዎች በተጨማሪ የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ የሚያደርጉ ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ብሬከሮችን (ጂአይኤስ) በቅርቡ በመትከል ወደ ሥራ ማስገባት እንደተቻለም አንስተዋል፡፡
እንደ አቶ ዝናቡ ገለፃ አሁን ያሉ ትራንስፎርመሮች ወደፊት ተጨማሪ ደንበኛ ቢመጣ ማስተናገድ ስለማይችሉ በየጊዜው እያደገ የሚመጣውን የኃይል አቅርቦት ፍላጎት በአስተማማኝ መልኩ ለመመለስ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያው ኢንቨስትመንትን በመሳብ በአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር ከማድረጉም ባለፈ የተቋሙ የግሪድ ሲስተም በቀለበት ስርዓት እንዲያያዝ በማድረግ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማከፋፈያ ጣቢያው የኦፕሬሽን ባለሙያው አቶ ወንደሰን ሲሳይ በበኩላቸው የማከፋፈያ ጣቢያው ለአካባቢው የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማደግ የሚኖረውን ሚና በመገንዘብ ያልተቆራረጠ የኃይል ፍሰት እንዲኖር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡


በቅርቡ በጣቢያው የተከሄዱ የአቅም ማሳደግ እና ብሬከር የማዘመን ሥራዎች የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ፣ የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራዎችን በቀላሉና በአጭር ጊዜ ለማከናወን እንዲሁም ኃይል ተቋርጦ የሚቆይበትን ጊዜ በማሳጠር የደንበኞቹን እርካታ ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለተጠቃሚው ያልተቆራረጠና የተመጣጠነ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማድረስ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም ባለሙያው አመለክተዋል፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው ከለገጣፎና ከአላማጣ ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር ኃይል ተቀብሎ በአምስት ባለ 33 እና በስድስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ለኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ካርቪኮ ለተሰኘ ፋብሪካ፣ ለኮምቦልቻ፣ ሀርቡ፣ ባቲ ከተሞች እና በዙሪያው ለሚገኙ አካባቢዎች እንዲሁም በከፍተኛ ወጭ መስመሮች ለሰመራ፣ ከሚሴ እና ኮምቦልቻ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል እያቀረበ ይገኛል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

