የኃይል አቅርቦት ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ረገድ ሚናው የጎላ ነው

የኃይል አቅርቦት ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ረገድ ሚናው የጎላ ነው

የኃይል አቅርቦት በኮምቦልቻ ከተማ በተኪ እና ወደውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማምረት ላይ ለተሰማሩ እንዲሁም ለፌደራል ለመንግስት ታክስ በመክፈል በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ በኩል ሚናው የጎላ እንደሆነ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ወንድወሰን ልሳነወርቅ እንዳስታወቁት በኮምቦልቻ ከተማ 127 ከፍተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ይገኛሉ፡፡

ከማህበረሰቡና ከመንግስታዊ ተቋማት በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙት የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ የአምራችና የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከፍተኛ የሆነ የኃይል ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በከተማዋ ከ12 እስከ 13 ሜጋ ዋት ኃይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ወንደሰን አንድ ኩባንያ በቀጣይ እስከ 250 ሜጋ ዋት የሚደርስ የኃይል ፍላጎት እንዳለው ጥያቄ ማቅረቡንም ተናግረዋል፡፡

የሚቀርቡ የኃይል ፍላጎቶችን ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ምክትል ከንቲባው በከተማዋ አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያዎች በተጨማሪ ባለ 400 ኪሎ ቮልት አዲስ የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎችን ለመመለስ በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራ እያከናወነ እንደሆነና በቅርቡ በኮምቦልቻ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የተከናወነው ሥራም በከተማዋ የነበረውን የኃይል መቆራረጥ ችግር በመቀነስ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኘው የኮምቦልቻ 3 ማከፋፈያ ጣቢያ ሲጠናቀቅ በከተማዋ ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት አቅም እንደሚፈጥርም አስታውቀዋል፡፡

ባለሀብቶች የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ያልተቆራረጠ ኃይል ማግኘት ይኖርባቸዋል ያሉት አቶ ወንድወሰን ፋብሪካዎች አሁን ያላቸውን የ59 በመቶ የማምረት አቅም ወደ 70 በመቶ ለማድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top