የአሶሳ 2 ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታን ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

የአሶሳ 2 ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታን ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከቻይናው ኖሪንኮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን ጋር የጉባ-አሶሳ 2 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የአሶሳ 2 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታን ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኖሪንኮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሚስተር ዱ ዢኦዶግ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት ተቋሙ ከተከዜ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጀምሮ በተለያዩ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ከኩባንያው ጋር አብሮ ሲሰራ ቆይቷል።

ስምምነቱ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝ የሚያደርግና ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ኩባንያው ግንባታውን በተያዘለት የጊዜ ገደብና በጀት በጥራት ለማጠናቀቅ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

ኩባንያው በሌሎች ሀገራት በኃይል ዘርፍ የሚያደርገውን ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያም ተግባራዊ በማድረግ በመንግስትና በግል አጋርነት በሚገነቡ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የኖሪንኮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሚስተር ዱ ዢኦዶግ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ለ30 ዓመታት ተሰማርቶ መቆየቱን ተናግረዋል።


ይህን የኩባንያውን የረጅም ጊዜ ልምድና አቅምን በመጠቀም ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ፣ በጀትና በጥራት አጠናቆ ለማስረከብ ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በሌሎች መስኮችም በስፋት ተቀራርበውና ተባብረው እንዲሰሩ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ደስታዓለም ኃይሉ በበኩላቸው አሁን ላይ የአሶሳ ከተማና አካባቢው ኃይል የሚያገኘው ከጊምቢ-መንዲ-አሶሳ ባለው መስመር መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ በዚህ መስመር ላይ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን የኃይል መቆራረጥ በማስወገድ አሶሳን ጨምሮ ክልሉ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጨማሪና አስተማማኝ ኃይል እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ህዳሴ ግድብን በ400 ኪሎ ቮልት ቀለበት(ሪንግ) መስመር በማገናኘት የኤሌክትሪክ ኔትወርኩን ለማጠናከር የጎላ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ከ121 ነጥብ 876 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለት የጠቆሙት አቶ ደስታዓለም አጠቃላይ ፕሮጀክቱን በ24 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

የጉባ አሶሳ 2 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት የአሶሳ 2 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያን ጨምሮ በጉባ የሚገኘውን የ400 ኪሎ ቮልት እና በነባሩ አሶሳ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚገኘውን የ132 ኪሎ ቮልት መስመር ግንባታና የማስፉፊያ ሥራዎች ያጠቃልላል።

Scroll to Top