በየዓመቱ ጳጉሜን 4 የተቋም ቀን ሆኖ ይከበራል – ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

በየዓመቱ ጳጉሜን 4 የተቋም ቀን ሆኖ ይከበራል – ኢንጂነር አሸብር ባልቻ


በየዓመቱ ጳጉሜን 4 የተቋም ቀን (Company Day) ሆኖ እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አስታወቁ።

ኢንጂነር አሸብር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሚከበርበት ሥነስርዓት ላይ እንደገለፁት ጳጉሜን 4 የሀገራችን ብሔራዊ አርማ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምረቃ የበቃበት ቀን በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም በዚሁ ዕለት በየዓመቱ የተቋም ቀን ሆኖ እንዲከበር ወስኗል።

በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከትንሽ ተነስተው ለታላቅነት የበቁት ባላቸው ፋይናንስ ሳይሆን በሠራተኞቻቸው የዘወትር ትጋትና ጥረት መሆኑን ገልፀው የተቋሙ ሠራተኞችም ለተቋሙ ስኬት ላበረከቱት ጉልህ አሰተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ተቋሙ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበበት ዓመት ከመሆኑም ባሻገር ለመጀመሪያ ጊዜ 39 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱንም ነው የተናገሩት።

የተቋሙ የማመንጨት አቅም በእጥፍ ጨምሮ 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት የደረሰውም በዚሁ 2018 በጀት ዓመት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህን ሁለንተናዊ ስኬት በማምጣት ረገድ በየሸለቆውና ባልተመቼ የስራ ከባቢ ሌት ከቀን የሚሠሩ የተቋሙ ሠራተኞች የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ የገለፁት ዋና አስፈጻሚው ተቋሙን በትጋት እና በቁርጠኝነት ለሚያገለግሉ ባለሙያዎች እና የስራ ኃላፊዎች እውቅናና ሽልማት መስጠት ተገቢ መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል።

የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማላቅና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት በማጠናቀቅ የበጀት ዓመቱን ግብ ማሳካት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

ኢንጂነር አሸብር አክለውም ተቋማዊ አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን ብሎም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በታዳሽ ኃይል ለማስተሳሰር ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኛ ማህበር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ወልዴ በበኩላቸው ተቋሙ ላስመዘገበው ስኬት የተቋሙ ሠራተኛ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ገልፀው ከዚህ ጎን ለጎን ለሠራተኛው ጥሩ የስራ ከባቢ መፍጠር፣ የስራ ላይ ደህንነቱን እና ጥቅማጥቅሙን ማስጠበቅ እንደሚገባ በአፅንኦት አሳስበዋል።

የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ 2018 በጀት ዓመት ለተቋሙ ልዩ የስኬት ዓመት እንደነበር የገለፁ ሲሆን የሠራተኛውን አንድነት በማጠናከር በ2019 በጀት ዓመት የተያዙ ዕቅዶችን በስኬት ለማጠናቀቅ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዛሬው ዕለት በተከበረው የተቋም ቀን የፈጠራ ስራ ላበረከቱ ባለሙያዎች እና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የስራ ክፍሎች የምስክር ወረቀት፣የገንዘብ ድጋፍ እና የተሽከርካሪ ሽልማቶች ተበርክተዋል።

Scroll to Top