ሪጅኑ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሥራ ክፍሎች፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎችና ሠራተኞች እውቅና ሰጠ

ሪጅኑ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሥራ ክፍሎች፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎችና ሠራተኞች እውቅና ሰጠ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ 2 ሪጅን በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሥራ ክፍሎች፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎችና ሠራተኞች በዛሬው እለት እውቅና ሰጠ፡፡

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ዘበርጋ እንዳስታወቁት በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ የጥገና ሠራተኞች፣ ለማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊዎች፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ሥራቸውን እያከናወኑ ላሉ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና ሌሎች በሪጅኑ ሥር ለሚገኙ የሥራ ክፍሎች እውቅና ተሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት በሪጅኑ በስርቆት ምክንያት ወድቀው በነበሩ  የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች መልሶ ግንባታ እና በማከፋፈያ ጣቢያዎች የማስፋፊያ ሥራዎች ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ  ሠራተኞች የምስክር ወረቀት እና የማበረታቻ ሽልማት መበርከቱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ለሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመር፣ ማከፋፈያ ጣቢያና ለሲቪል ጥገና  እንዲሁም ለፋይናንስና አስተዳደር ቢሮዎች ለኃይል ማስተላለፍና ማከፋፈል ሥራዎች ለባረከቱት አስተዋጽኦ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ  በሪጅኑ ሥር ከሚገኙ 19 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ በኦፕሬሽንና በመለስተኛ ቅድመ ብልሽት ጥገና ሥራ እንዲሁም በማከፋፈያ ጣቢያ አስተዳደር የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው ለኮየ አቦ፣ ገላን እና ቢሾፍቱ 3 ማከፋፈያ ጣቢያዎች የምስክር ወረቀት እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል።

አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ኃይል የማከፋፈል ሥራቸውን በብቃት እያከናወኑ ለሚገኙት የመተሃራ ማከፋፈያ ጣቢያ ሠራተኞች በልዩ ሁኔት እውቅና በመስጠት የምስክር ወረቀት እና የማበረታቻ ሽልማት ስለመበርከቱም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የተቋሙን መሰረተ ልማት ደህንነት ቁጥጥር ከማስጠበቅ አኳያ ሪጅኑ ያመዘገበውን የላቀ አፈጻጸምና ስኬት መነሻ በማድረግ ለሪጅኑ የመሰረተ ልማት ደህንነት ኃላፊ እውቅና እንደተሰጣቸውም ነው የገለፁት።

መርሃ ግብሩ ሠራተኛው ላከናወነው ሥራ እውቅና በመስጠት በቀጣይ የተሻለ ሥራ እንዲያከናውን ለማበረታት እና በሠራተኛው መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነትና የትብብር መንፈስን ለማጠናከር እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

ረጅኑ በትላንትናው ዕለት በተቋም ደረጃ የተሰጠው እውቅና የሁሉም ሠራተኛ ውጤት መሆኑን ያነሱት አቶ አለማየሁ ሪጅኑ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሠራተኞችና የሥራ መሪዎችንም አመስግነዋል።

በቀጣይ በተቋምና በሪጅን ደረጃ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም ሠራተኛ የሥራ ላይ ደህንነትን በማክበርና የቡድን ሥራን እንደ መርህ በመያዝ  በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

Scroll to Top