የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከእጥፍ በላይ በማሳደግ የቀጣናውን የኃይል ትስስር እያጠናከረ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገለፁ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ለኢዚአ እንደገለጹት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ጽናት፣ አንድነትና ቁርጠኝነት በተግባር የተገለጠበት «ዳግማዊ ዓድዋ» ነው።
የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የላቀ ስኬት ማስመዝገብ እንደምትችል ለዓለም ያስመሰከረችበትና አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተችበት ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የግድቡ ተጠናቆ ወደ ኦፕሬሽን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱን የኃይል ማመንጨት አቅም እና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን አብራርተዋል።
ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ ካገኘው ከፍተኛ ገቢ በተጨማሪ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ማግኘቱን የጠቆሙት ኢንጂነር አሸብር ለዚህ ታሪካዊ ስኬት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ተቋሙ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዕዳ ተላቆ ወደ ትርፋማነት እንዲሸጋገር ማስቻሉን ጠቁመዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም የግድቡ ወደ ኦፕሬሽን መግባት ለቀጣናዊ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትስስር ማደግ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛልም ብለዋል።
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ለኬንያ እና ለጅቡቲ እንዲሁም በከፊል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ መሆኗን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ወደ እነዚህ ሀገራት ከሚላከው አጠቃላይ ኃይል ውስጥ 52 በመቶ የሚሆነው ድርሻ ከህዳሴው ግድብ የሚመነጭ መሆኑን አመልክተዋል።