በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ያለውን እምቅ የኤሌክትሪክ ሀብት በስፋት በማልማትና የሀገራትን የኤሌክትሪክ ግሪድ በማስተሳሰር ለቀጣናው ልማት ማዋል እንዲቻል የሀገራት የጋራ ቁርጠኝነትና ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ።
በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር አባል ሀገራት መካከል ያለውን የኃይል አቅርቦት፣ ፍጆታ እና ትስስር ለማጠናከር የተዘጋጀው የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል እየተካሄደ ነው።



በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ስቲሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር አሸብር ባልቻን ወክለው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ኢንጂነር ያለውአይቀር ማንደፍሮ እንደገለፁት የሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI) የኤሌክትሪክ ኃይል እና የዘመናዊ ዕድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር እየሆነ መጥቷል፡፡
ይሁንና በቀጣናው በሚገኙ ማህበረሰቦችና ኢንዱስትሪዎች ዘንድ የኃይል እጥረትና የአስተማማኝነት ችግር አሁንም ከባድ ፈተና እንደሆነ ቀጥሏል።
ቀጣናው የታዳሽ ኃይል ሀብት እጥረት እንደሌለበት የጠቆሙት ኢንጂነር ያለው ኢትዮጵያ በውሃ ኃይል፣ ኬንያ በጂኦተርማል፣ እንዲሁም የቀጣናው ሀገራት በንፋስና በፀሐይ ኃይል የበለፀጉ መሆናቸውን በአብነት አንስተዋል።
የተፈጥሮ ሀብቱ መኖሩ ብቻውን የኤሌክትሪክ አቅርቦትን የማያረጋግጥ በመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት የሚመጣው ኃይሉን በማልማትና የማስተላለፊያ አውታሮችን በማስፋፋት ከማህበረሰቡ ጋር ማገናኘት ሲቻል እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ኢንጂነር ያለውአይቀር አክለውም በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት አማካይነት እየተከናወነ ያለው የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ ኤሌክትሪክ በአንድ ሀገር ድንበር ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከሀገር ወደ ሀገር በመሻገር ኢንዱስትሪዎችንና ከተሞችን የሚያንቀሳቅስ መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።
ይህ የኃይል ትስስር አንዱ ሀገር ትርፍ ኃይል ሲኖረው የኃይል እጥረት ያለበትን ጎረቤት ሀገር ወዲያውኑ ለመደገፍና የንግድ ወጪን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በቀጠናው የተቀናጀ፣ ንፁህና አስተማማኝ የኃይል ፍሰት እንዲኖር የጋራ ራዕይ ሰንቆ መስራት እንደሚገባ የገለጹት ኢንጂነር ያለውአይቀር በቀጣናው ወጥ የኤሌክትሪክ ገበያ እውን ለማድረግ ሀገራት ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ባለፉት ዓመታት በአባል ሀገራቱ የተከናወኑ የቴክኒክ ሥራዎች የሚዳሰስ ውይይት የሚደረግ ሲሆን ኤልኒኖ በሀገራቱ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እና ሀገራቱ ያላቸውን ዝግጁነት የሚያሳይ ሪፖርት እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በምስራቅ አፍሪካ የኃይል መረብ (Grid) ላይ ያጋጠሙ ችግሮች፣ መንስኤዎቻቸው እና የወደፊት አዝማሚያዎች ከየሀገራቱ በተሰበሰቡ መረጃዎች መሠረት የተቀናጀ ግምገማ እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል።






