የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት አስር ዓመታት ለጎረቤት ሀገራት ኤክስፖርት ያደረገው ኃይል የ31 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታወቀ።
በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር አባል ሀገራት መካከል ያለውን የኃይል አቅርቦትና የገበያን ትስስር ለማጠናከር እንዲሁም በቀጣናው በሚጠበቀው የኢል ኒኖ ስጋት መከላከል ዙሪያ ለመምከር የተዘጋጀው የምክክር ጉባኤ ተጠናቋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳይሬክተር ኢንጂነር ሚኪያስ ወንድሙ ስለሀገሪቱ የኃይል ማምረት አቅም እና የኃይል ኤክስፖርት ዕድገት ለቀጣናው ሀገራት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ የኃይል ምርት ውስጥ የኤክስፖርት ድርሻው ከ6.5 እስከ 10 በመቶ ይደርሳል።
የምስራቅ አፍሪካን የኃይል ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ሰፊ ዕቅዶች መያዛቸውን ያብራሩት ኢንጂነር ሚኪያስ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ የኃይል ኤክስፖርት አቅምን ወደ 5 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም የኃይል ሽያጭ ንግድን ለማስፋት ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ከሶማሊላንድ ጋር አዳዲስ የማስተላለፊያ መስመሮችን የመዘርጋት እንዲሁም ከጂቡቲና ከሱዳን ጋር ሁለተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የመገንባት ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
የሀገሪቱ የኃይል ማመንጨት ሥርዓት ከ95 በመቶ በላይ በውሃ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የኃይል ስብጥርን ለማስፋት የሚያስችሉ ዕቅዶች ተቀርፀው እየተተገበሩ መሆናቸውን ኢንጂነር ሚኪያስ ገልፀዋል።
የሀገሪቱ የኃይል ማመንጨት ሥርዓቱ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ውስጥ እንዳይገባ የኃይል ስብጥርን ለማስፋት የሚያስችሉ ዕቅዶች ተቀርፀው እየተተገበሩ መሆናቸውንም ኢንጂነር ሚኪያስ አክለው ገልፀዋል።


