ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ልታሳድግ ነው

ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ልታሳድግ ነው

ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችላትን ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀች መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የኃይል ትስስር የበለጠ ለማጠናከርና የኃይል ኤክስፖርት አቅሟን ለማሳደግ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ስታካሂድ የነበረው የምክክር መድረክ ተጠናቋል፡፡

በተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ደስታለም ኃይሉ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 200 ሜጋ ዋት ኃይል ለኬንያ እያቀረበች ነው።

በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተከናወኑ ያሉ የቴክኒክና መሰል ሥራዎችን በማጠናቀቅ ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ የሚቀርበው የኃይል መጠን ወደ 400 ሜጋ ዋት ያድጋል።

ይሁንና ተጨማሪ ኃይል ከመላኩ በፊት የሙከራ ሥራውን የሚያከታተል የጋራ የቴክኒክ ቡድን ወደ ሥራ መግባቱን ኢንጂነር ደስታለም ጠቁመዋል።

የኬንያ ኤሌክትሪክ ግሪድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የግሪድ አለመረጋጋት እንዳይከሰት የጋራ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሙከራ ደረጃ 100 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለታንዛኒያ እያቀረበች በመሆኑ በኬንያና ታንዛኒያ መካከል ያለው የመሠረተ ልማት ማሻሻያ ሲጠናቀቅ መደበኛ የኃይል ሽያጭ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም አዳዲስ የማስተላለፊያ መስመሮችን በመዘርጋትና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን በመገንባት ከቀጣናው ሀገራት ጋር የሚደረገውን የኃይል ኤክስፖርት  ትስስር ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረገው የኃይል ትስስርና ትብብር የቀጣናውን የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ተዳራሽነት ለማሻሻል እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትልቅ መሠረት እንደሆነ አስረድተዋል።

Scroll to Top