በግንባታ ላይ የሚገኘው የአሰላ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በከፊል ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ ለተቋሙ የኃይል ምርት መጨመር ምክንያት ሆኗል።
በፕሮጀክቱ የኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ መስፍን መስቀሌ እንደገለፁት በግንባታ ላይ የሚገኘው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከግንቦት 6 ቀ 2017 ዓ.ም ጀምሮ በከፊል ኃይል ሲያመነጭ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅትም በፕሮጀክቱ ከተተከሉት 29 የንፋስ ተርባይኖች መካከል 10ሩ በተለያዩ ጊዜያት ከዋናው የኃይል ቋት (ግሪድ) ጋር ተገናኝተው ኃይል እያመነጩ ይገኛሉ። ይህም ፕሮጀክቱ ባለፉት ሁለት ወራት 8 ነጥብ 9 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለተቋሙ ተጨማሪ የኃይል ምርት ማስገኘቱን ገልፀዋል።
ከፕሮጀክቱ የሚመነጨውን ኃይል ከመልካ ዋከና ኃይል ማመንጫ እና ከበቆጂ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር በማጣመር ወደ ግሪዱ እንዲተላለፍ የሚከናወንበት የኦፕሬሽን ሂደት ቀድመው ከተገነቡ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ልዩ እንደሚያደርገው የተናገሩት አቶ መስፍን የየኦፕሬሽን ሥራውን በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ዘመናዊ የዲጂታል መሳሪያዎች የተገጠሙለት ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል።
በፕሮጀክቱ የሱፐርቪዥን ቴክኒሺያን የሆኑት አቶ መንግስቱ ድሌ በበኩላቸው የተርባይን ተከላና የኬብል ዝርጋታ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የተርባይኖች የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ኃይል ለማመንጨት ዝግጁ መሆናቸውን በፍተሻና ሙከራ በማረጋገጥ ተርባይኖቹን በሂደት ወደ ኦፕሬሽን የማስገባቱ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በዚህም እስከ አሁን 10 ተርባይኖችን በከግሪድ ጋር ማገናኘት የተቻለ ሲሆን በቀጣይ የሙከራና የፍተሻ ሥራዎችን በጥንቃቄ በማከናወን በየቀኑ አንድ ተርባይን ወደ ኦፕሬሽን ለማስገባታ ታቅዶ እየተሰራ ነው።
ቀሪ ተርባይኖችን በቀጣዩ አንድ ወር ውስጥ ወደ ኦፕሬሽን ለማስገባት ሥራ ተቋራጩ ተጨማሪ ባለሙያዎችን ከመመደብ ጀምሮ በፕሮጀክቱ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
የሙከራና የፍተሻ ሥራቸው የተጠናቀቁ ተርባይኖች በሂደት ተራ በተራ ቀድመው ኃይል ወደ ማመንጨት ሥራ እንዲገቡ መደረጉ ያለውን የንፍስ ኃይል በመጠቀም ሲስተሙን ለመደገፍ እና የግሪዱን አቅም ለማረጋጋት እንደሚያግዝም የሥራ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።
ሁሉም የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ሲጀምሩ ሀገሪቱ ከንፋስ የምታገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ 544 ሜጋ ዋት ከፍ በማድረግ የኃይል ስብጥሩን ለማመጣጠን ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




