የአርባ ምንጭ 2 ማከፋፈያ ጣቢያ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

የአርባ ምንጭ 2 ማከፋፈያ ጣቢያ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በቅርቡ ከብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ግሪድ ጋር እንደሚገናኝ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የምዕራፍ አንድ ሳይት ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ አበበ ሚጀና እንዳስታወቁት የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ 82 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች 90 በመቶ ተጠናቀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የመጀመሪያና የሁለተኛ ሙከራና ፍተሻ ሥራዎች መከናወናቸውን የገለፁት አቶ አበበ አሁን ላይ እየተከናወኑ ያሉ የማጠናቀቂያ ሙከራና ፍተሻ ሥራዎች በቅርቡ ተጠናቀው ጣቢያው ከብሔራዊ ግሪድ ጋር እንደሚገናኝም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 1 የማስተላለፊያ መስመር ሥራ 95 በመቶ መጠናቀቁን አንስተው የአርባ ምንጭ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ ማስፋፊያ የሙከራና ፍተሻ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የመስመሩ የሙከራና ፍተሻ ሥራዎች ከጥቃቅን የማስተካከያ ሥራዎች በስተቀር መጠናቀቃቸውን እና በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የኤሌክትሪካል መሀንዲስ ፍራኦል ዳዲ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ የሙከራና ፍተሻ ሥራዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን መሠረት ባደረገ መልኩ ላለፉት ሦስት ወራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

በፍተሻና ሙከራ ሥራዎች ላይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች መሳተፋቸውንና ከዚህም ተቋሙ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ግብዓት የሚሆን ልምድ እና ተጨማሪ እውቀት መገኘቱን አቶ ፍራኦል አስረድተዋል።

ከዕቃ ማጓጓዝ እስከ ተከላ ያሉ የአሰራር ሂደቶች በተቀመጠው የስምምነት ሰነድ መሠረት መፈፀማቸውንና እያንዳንዱ ዕቃ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ እና እያንዳንዱ ዕቃዎች በውሉ ላይ በተቀመጡ መመዘኛ መስፈርቶች መሠረት እንዲፈፀሙ በተለያዩ መመዘኛ መስፈርቶች በመከታተል እና ችግሮች ሲስተዋሉም የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግ በጥራት መከናወኑን የተናገሩት ደግሞ የፕሮጀክቱ አማካሪ ሱፐርቫይዘር አቶ ብርሃኑ ባህሩ ናቸው።

የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ 476 ሜጋ ቮልት አምፔር የመሸከም አቅም ያላቸው ስድስት ትራንስፎርመሮች እንዲሁም አንድ ባለ 132፣ አስር ባለ 33 እና አምስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች አሉት።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top