የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ኃይል ማመንጨት ጀመረ

የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ኃይል ማመንጨት ጀመረ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሦስት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።

የፕርጀክቱን የግንባታ ሂደት እና የኃይል ማመንጨት የመጀመር ሥራ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ የደንማርክ አምባሳደር ሚስተር ሱነ ክሩግስትረፕ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ፕሮጀክቱን ፋይናንስ የሚያደረገው የዳኒሽ ባንክ ተወካዮች ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ እና የኃይል ስብጥርን ለማመጣጠን ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም ኢትዮጵያ የኃይል ስብጥር ላይ ትኩረት ለማድረጓ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረትና የደንማርክ መንግስትም በኃይል ልማት ዘርፉ ላይ እያደረጉት ካለው ድጋፍ ባለፈ ለሌሎች መሠረተ ልማቶች ድጋፍ በማድረግ ለሀገሪቱ እድገት የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የትብብር ሥራው ታዳሽ ኃይል ወደ ግሪድ በማስገባት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ሚስተር ቪንሰንት ቪያዉድ በበኩላቸው አሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ልማት ለሰጠችው ትኩረት አመላካች መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይ ኢትዮጵያ በኃይል ልማት ዘርፉ ለምታከናውናቸው ሥራዎች ህብረቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የደንማርክ አምባሰደር ሚስተር ሱነ ክሩግስትረፕ እንደተናገሩት የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በኢትዮጵያና በደንማርክ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ብለዋል፡፡

ሀገራቸው በንፋስ ኃይል ማመንጫ ያላትን ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ እያካፈለች እንደምትገኝ ገልፀው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ላይ ያደረገችው ድጋፍም ለዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የኃይል መሠረተ ልማት ቁልፍ መሳሪያ እንደሆነ  በመገንዘብ የደንማርክ መንግስት  ለፕሮጀክቱ ካደረገው የመዋዕለ ነዋይ ድጋፍ በተጨማሪ የግንባታ ሥራውን በቅርበት ሲከታተል እንደነበር አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደተናገሩት በሀገሪቱ ያለውን የኃይል ተደራሽነት ለማስፋፋት በርካታ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ይገኛሉ።

የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ማመንጨት እንዲጀምር የአውሮፓ ህብረትና የደንማርክ መንግስት ላደረጉት ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ጉብኝቱ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ ያደረጉ አካላት ፕሮጀክቱ የደረሰበትን የግንባታ እና የመጀመሪያውን ኃይል የማመንጨት ሂደት በማየት ለቀሪ ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ጉብኝቱ በቀጣይ በአካባቢው ለመገንባት ለታሰበው ተመሳሳይ ፕሮጀክት ድጋፍ የሚያደርጉበትን ዕድል እንደሚፈጥርም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ፕሮጀክቱ ስለደረሰበት ሂደትና ስለተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች እንዲሁም በግንባታ ሂደት እያጋጠሙ ስላሉ ችግሮች በፕሮጀክቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ገለፃ ተደርጓል።

ፕሮጀክቱ ከሚኖሩት 29 ተርባይኖች መካከል ዛሬ ሦስቱ ኃይል ማመንጨት የጀመሩ ሲሆን በቀጣይም ሌሎቹ ተርባይኖች ኃይል ወደማመንጨት ሥራ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስና ትክክለኛ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top