ማከፋፈያ ጣቢያው የኃይል ብክነትን በማስወገድ አስተማማኝ ኃይል እያቀረበ  ነው

ማከፋፈያ ጣቢያው የኃይል ብክነትን በማስወገድ አስተማማኝ ኃይል እያቀረበ  ነው

የአዳማ አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ የኃይል ብክነትን በማስወገድ አስተማማኝ ኃይል እያቀረበ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ብርሃኑ ቦንገር እንደገለፁት ጣቢያው ለአዳማ ከተማ እንዲሁም የአዳማ ቆርቆሮን ጨምሮ በዙሪያዋ ለሚገኙ በርካታ ፋብሪካዎች ኃይል እያቀረበ ይገኛል።

ከከተማዋ መስፋፋትና ከኢንዱስትሪዎች ፍሰት መጨመር ጋር ተያይዞ እየቀረበ ያለውን የኃይል ጥያቄ ለመመለስ ተጨማሪ ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር ተንቀሳቃሽ የማከፋፈያ ጣቢያ  እንደተተከለለት ተናግረዋል።

በዚህም ከ80 ሜጋ ዋት በላይ በመጫን ቀደም ሲል ጣቢያው የነበሩትን ሰባት ወጭ መስመሮች ወደ 13 በማሳደግ ለአዳዲስ እና ተጨማሪ ኃይል ለሚጠይቁ ነባር ደንበኞች አስተማማኝ ኃይል ማቅረብ እንደተቻለ  ጠቁመዋል።

ለደንበኞች ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳማ ዲስትሪክት ጋር በመተባበር የስካዳ ሥርዓት መተግበሩንም ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ጣቢያው ከ90 በመቶ በላይ የአዳማን የኃይል ፍላጎት ሲያሟላ መቆየቱን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ አሁን ላይ የአዳማ ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ተገንብቶ ወደ ሥራ በመግባቱ በጣቢያው ላይ የነበረውን ጫና እንዲቀንስ አድርጎታል ብለዋል።

የጣቢያውን ኃይል ጭነት እና ፍሰት የሚቆጣጠሩና ብክነትን የሚቀንሱ ሦስት “ፓወር ሪአክተሮች” መተከላቸውን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያውን ደህንነት ለማረጋገጥ የመቆጣጠሪያ ክፍሉን የማሻሻልና የማዘመን ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የመቆጣጠሪያ ቅየራው ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ክብሮም በረኼ በበኩላቸው የጣቢያው የመቆጣጠሪያ ሥርዓቶች ረጅም ዓመት ያገለገሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሲ ዋይ ጂ በተባለ የቻይና ኩባንያ አማካኝነት በአዲስ መልክ የመቀየር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም በተለያየ ምክንያት ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን በመከላከል የኃይል መቆራረጡን ለማስወገድ እና የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማዘመን እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

አዳማ አንድ ማከፋፈያ ጣቢያ ከአዋሽ ሰባት፣ ከቆቃ እና ከአዳማ 2 ንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ኃይል ይቀበላል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top