የኒውክሊየር ልማት የኢነርጂ ደህንነትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው

የኒውክሊየር ልማት የኢነርጂ ደህንነትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው

የኒውክሊየር ልማት የኃይል ስብጥሩን በማሳደግ የኢነርጂ ደህንነትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ ገለጸ፡፡

በዘርፉ የኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያለውአይቀር ማንደፍሮ እንደገለጹት የኢትዮጵያ መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ጨምሮ በርካታ ጥቅሞች ያሉትን የኒውክሊየር ኃይል ለማልማትና ለመጠቀም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡

ተቋሙ በ2012 ባስጠናው የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ ካስቀመጣቸው አራት አማራጮች አንዱ የኒውክሊየር ኃይል ለማልማት የነበረ ቢሆንም ከሚጠይቀው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አንጻር ለሌሎቹ አማራጮች የበለጠ ትኩረት መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም አሁን ላይ በመንግሥት የተሰጠውን የትኩረት አቅጣጫና እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት አስተማማኝ በሆነ መልኩ ምላሽ ለመስጠት ተቋሙ በራሱ የፋይናንስ አቅም የቀጣይ 25 ዓመት የኃይል ልማት ዕቅዱን ለመከለስ የአማካሪ ቅጥር እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ያሉት የኃይል አማራጮች በተፈጥሮ ላይ ጥገኛና ለተለያዩ የተፈጥሮ ክስተቶች ተጋላጭ የሆኖ ናቸው ያሉት ሥራ አስኪያጁ የኒውክሊየር ኃይል ግን የአየር ንብረት ተጽዕኖን የሚቋቋም እና በከፍተኛ አቅም ያለማቋረጥ ኃይል ማመንጨት የሚችል አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።

የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫዎች አነስተኛ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ያላቸው በመሆኑ ለአየር ንብረት ጥበቃ ተመራጭ መሆናቸውንና ከኤሌክትሪክ በተጨማሪ ለኢንዱስትሪዎች የሚሆን እንፋሎት ለማቅረብ እንደሚያስችሉ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ እስከ 2034 ድረስ ከኒውክሊየር ኃይል ከ1,200 እስከ 2,400 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት ግብ መቀመጡን  ጠቅሰዋል።

ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስፈላጊውን ድጋፍና ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱንና ከኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።

ተቋሙ የኒውክሊየር ኃይልን ጨምሮ ከተለያዩ አማራጮች ኃይል ለማመንጨትና የኃይል ምንጮችን ለማስፋት በትኩረት እየሠራ መሆኑን የገለፁት አቶ ያለውአይቀር ለዚህም የአዋጭነት ጥናት የተከናወነላቸውን ፕሮጀክቶች በወቅቱ ወደ ትግበራ ለማስገባትም በራስ አቅም የሚከናወኑትንና በአጋር አካላት የሚለሙትን የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ95 በመቶ በላይ የሆነውን የውሃ ኃይል ማመንጫ ድርሻን የፀሐይ ፣ የጂኦተርማልና የንፋስ ኃይልን በስፋት ወደ ሥራ በማስገባት ወደ 70 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እየተሠራ ቢሆንም ዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ መተግበር እንዳልተቻለ አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ በኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ዘርፍ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ እንዲሁም ከግንባታና ከደህንነት ጋር የተያያዙ ሥጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከተለያዩ አማራጮች ከሚመነጨው ኢነርጂ ውስጥ የኒውክሊየር ኃይል ድርሻ ከ10 በመቶ ያልበለጠ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
‎ 
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top